አውስትራሊያዊው ተናካሽ ቁራ ሲሸሽ ከብስክሌት ወድቆ ሞተ

የ76 ዓመቱ አውስትራሊያዊው ከተናካሽ ቁራ እራሱን ለማዳን ሲሸሽ ከብስክሌት ላይ ወድቆ ህይወቱ አለፈ።

ፖሊስ እንዳለው ብስክሌት ሲጋልብ የነበረው አዛውንት ከአደገኛው ወፍ ለማምለጥ ጥረት ሲያደርግ መንገድ ስቶ ከፓርክ አጥር ጋር ተጋጭቶ ህይወቱ አልፏል።

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ህይወቱን ለማዳን ብዙ ጥረት ቢያደርጉም ጭንቅላቱ ላይ የደረሰበት ጉዳት ከባድ ስለነበር ህይወቱን ማትረፍ አልተቻለም።

በአውስትራሊያ ጥቁር እና ነጭ ቀለም ያላቸው ቁራዎች በፍጥነት እየበረሩ በእግረኞች እና ብስክሌት በሚጋልቡ ሰዎች ላይ ጉዳት የማድረሳቸው ዜና የተለመደ ነው።

በፓርኩ አቅራቢያ በወፎቹ በርካታ ተመሳሳይ ጥቃቶች መድረሳቸውን የአከባቢው መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት አእዋፋቱ በመራቢያቸው ወቅት በአካባቢያቸው የሚገኝ ማንኛውንም እንስሳ ያጠቃሉ። ከፈረንጆቹ ሞቃታማ ወራት በኋላ በሚኖሩት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ደግሞ የአዋፋቱ ጥቃት ይጨምራል።

በሲድኒ ከተማ የሚገኝ የአንድ አካባቢ ምክር ቤት በሰዎች ላይ ጥቃት እያደረሱ የሚገኙ ቁራዎችን ለመግደል ውሳኔ ማስተላለፉ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

የአውስትራሊያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እንደዘገበው ሌላ አንድ ነዋሪ ከቁራው ለመሸሸ ረዥም ሰዓት መሮጡን ተከትሎ ባጋጠመው የልብ ህመም ለሆስፒታል አልጋ ተዳርጓል።