ለዓመታት ወንድ ልጅ ያልተወለደባት ከተማ

ወንድ ልጅ ከተወለደ ዓመታት የተቆጠሩባት በደቡብ ፖላንድ የምትገኝ አንዲት ትንሽ ከተማ ከንቲባ፤ ወንድ ልጅ ለሚወልዱ ጥንዶች ሽልማት እንደሚሰጡ አሳወቁ።

በከተማዋ ወንድ ልጅ ከተወለደ አስር ዓመት ሊሆን የተቃረበ ሲሆን ይህም የከተማዋን አስተዳዳሪ ሳያሳስባቸው አልቀረም።

እምብዛም የዜና ርዕስ ሆና የማታውቀው ሚየሲች ኦድርዛንሰኪ የተባለችው ከተማ የወንድ ልጆች መወለድን ለማበረታታት በወሰደችው እርምጃ መነጋገሪያ ሆናለች።

አንድ መቶ ያህል ቤቶች ብቻ ያሏት ይህች ከተማ ሰፋፊ የእርሻ መሬት የሚገኝባት ሲሆን፤ ህጻናትን ለማሳደግ አመቺ ቦታ ናት ተብሎ ይታሰባል። ነገር ግን ባለፉት ዓመታት የአካባቢውን ነዋሪ ያሳሰበው ነገር የተወለዱት ህጻናት ሴቶች ብቻ መሆናቸው ነው።

በከተማዋ ያለው የወሊድ መጠን እጅግ በጣም አነስተኛ የሚባል ሲሆን፤ የመጨረሻው ወንድ ልጅ ከተወለደ በኋላ ባሉት ዓመታት ውስጥ 12 ህጻናት የተወለዱ ሲሆን ሁሉም ሴቶች ናቸው ተብሏል።

የወንዶች ቁጥር መቀነስ ጉዳይ በስፋት ትኩረት ያገኘው በከተማዋ የሚገኙ ሴቶች አንድ የበጎ ፈቃድ የእሳት አደጋ ሠራተኛን አሰልጣኛቸው እንዲሆን ከጠየቁት በኋላ ነው። ሴቶች ብቻ የሆኑበት የከተማው ቡድን አካባቢያዊ ውድድሮችን ካሸነፉ በኋላ ጋዜጠኞችና ተመራማሪዎች ጥያቄ በማንሳታቸው ጉዳዩ ትኩረት ማግኘቱም ተጠቅሷል።

የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ከንቲባ ራጅሙንድ ፍሪችኮ እንደተናገሩት፤ በጉጉት የሚጠበቀው ወንድ ልጅ ድንቅ ሽልማት የሚበረከትለት ሲሆን አንድ ዛፍ በስሙ ይሰየምለታል።