የዚምባብዌ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ሆስፒታል ከገቡ ወራት እንዳለፋቸው ተነገረ

የዚምባብዌ የቀድሞ መሪ ሮበርት ሙጋቤ ላለፉት አራት ወራት በሲንጋፖር ሆስፒታል ውስጥ ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኙ የአገሪቷ ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ገለፁ።

የ95 ዓመቱ የእድሜ ባለፀጋ -ሙጋቤን " የአገራችን መሥራች አባትና ባለውለታ" ያሏቸው ፕሬዚዳንት ምናንጋግዋ የቀድሞው ፕሬዚደንት ምንነቱ ባልተገለፀ ሕመም በሲንጋፖር የሕክምና ክትትል እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባለፈው ሰኞ ባወጡት መግለጫ እንዳሉት ሮበርት ሙጋቤ በየጊዜው ከሚያደርጉት የጤና ምርመራ በተጨማሪ በሆስፒታል ሆነው የቅርብ ሕክምና ክትትል እንዲያደርጉ ሐኪማቸው መወሰናቸውን ገልፀዋል።

ፕሬዝዳንት ምናንጋግዋ፤ ሙጋቤ በጤናና በእርጅና ምክንያት መራመድ እንደተሳናቸው ባለፈው ሕዳር ወር አስታውቀው ነበር።

ባለፈው መጋቢት ወርም የቀድሞ ፕሬዝዳንቱ ለሕክምና ወደ ሲንጋፖር እንዳመሩና በግንቦት ወር አጋማሽ ወደ ሀገራቸውን እንደሚመለሱ ማስታወቃቸው ይታወሳል። ይሁን እንጂ ሮበርት ሙጋቤ አሁንም በሆስፒታል ውስጥ እንደሚገኙ ተገልጿል።

ባለፈው ሳምንት ሙጋቤን ለመጠየቅ ወደ ሲንጋፖር ቡድን እንደላኩ የተናገሩት ፕሬዝዳንት ምናንጋግዋ የጤና መሻሻል እያሳዩ እንደሆነና በቅርቡ ተሽሏቸው ከሆስፒታል ሊወጡ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

በዚምባብዌ የሕብረተሰብ ጤና አገልግሎት በመዳከሙ የገንዘብ አቅም ያላቸው ሰዎች ወደ ደቡብ አፍሪካና ሌሎች አገራት በመሄድ ለመታከም ይገደዳሉ።

ሮበርት ሙጋቤም በሥልጣን ላይ በነበሩ ጊዜ የሕክምና ክትትላቸውን የሚያደርጉት በሲንጋፖር ነበር።

ፕሬዚዳንት ምናንጋግዋ ለ37 ዓመታት አገሪቷን ሲመሩ ከነበሩት ሮበርት ሙጋቤ እአአ ሕዳር ወር 2017 ላይ ሥልጣን መረከባቸው ይታወሳል።