ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፌስ ቡክ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን የፕሮፓጋንዳ ገጾች አገደ
ፌስቡክ ከሳዑዲ መንግሥት ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸው ሰዎች ሐሰተኛ አካውንቶች በመክፈት ገጹን ፕሮፓጋንዳ ለመንዛት እየተጠቀሙበት መሆኑን ደርሼበታለሁ አለ።
የፕሮፓጋንዳ ዘመቻው ትኩረት ያደረገው መካከለኛው ምስራቅንና ሰሜን አፍሪካን ሲሆን አብዛኛዎቹ ይዘታቸው የሚቀርበው በአረብኛ እንደሆነ ተገልጿል።
ከ350 በላይ ገጾች መዘጋታቸውን የገለጸው ፌስ ቡክ፤ ከመንግሥት ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን ገጾችን በይፋ ከመንግሥት ጋር ግንኙነት አላችሁ ሲል ብዙ ጊዜ አይሰማም ነበር።
በዚህ ጉዳይ ላይ ሳዑዲ አረቢያ ለጊዜው ዝምታን መርጣለች።
ፌስ ቡክ በመግለጫው ላይ በዚህ ሳምንት የወሰደው ርምጃ እርሱ በሚያስተዳድራቸው በፌስ ቡክም ሆነ በኢንስታግራም ላይ "የተደራጀና ያልተገባ ባሕሪን" ለመከላከል መሆኑን ገልጿል።
እነዚህ ገጾች የተከፈቱት የየሀገራቱ ዜጎች የሀገራቸው የዜና አውታር ገጽን እንዲመስላቸው ተደርገው የተደራጁና የተከፈቱ ናቸው ሲል አትቷል።
ፌስቡክ ሐሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ ገጾችን በመከላከል ረገድ ኋላቀርነት አለበት በሚል ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል።
ድርጅቱ አክሎም ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ባይኖራቸውም ሐሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ ያላቸውንና በተባበሩት የአረብ ኤምሬትና ግብፅ የተከፈቱ ገጾችንም መዝጋቱን አስታውቋል።
የፌስ ቡክ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ የበላይ ኃላፊ እንዳብራሩት ከሆነ " ገጾቹን የሚያስተዳድሩ አካላት በአረብኛ አካባቢውን የሚመለከት ዜናና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን አንስተው፣ ስለ ልዑል ሞሐመድ ቢን ሰልማን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተሐድሶ፣ ስለሳዑዲ ጦር ስኬት፣ በይበልጥ ደግሞ በየመን ግጭት ወቅት ስላለው የሚጽፉ ናቸው" ብለዋል።
"ምንም እንኳ እነዚህ ሰዎች ማንነታቸው ለመደበቅ ቢሞክሩም ባደረግነው ጥናት ግለሰቦቹ ከሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ደርሰንበታል" ሲሉ አክለዋል።
እነዚህ ፌስቡክ ያገዳቸውን ገጾች 1.4 ሚሊየን ሰዎች ይከተሏቸው ነበር።
ፌስቡክ እንዳለው ከሆነ ዘመቻው ለማስታወቂያ ብቻ 108 ሺህ ዶላር ያወጣል።