በቄለም ወለጋ ዞን የደህንነት ባለሙያ በታጣቂዎች ተገደሉ

በምዕራብ ኦሮሚያ ቄለም ወለጋ ዞን በየማለጊ ወለል ወረዳ የፀጥታና የደህንነት ባለሙያ አቶ ጫላ ነገሪ በታጣቂዎች ትላንት ሐምሌ 4፣2011ዓ.ም ተገደሉ።

የዞኑ የፀጥታና አስተዳዳሪ ምክትል ኃላፊ አቶ መሀመድ ቦሩ ለቢቢሲ እንደገለፁት ግለሰቡ ከደምቢዶሎ ወደ ተጆ በህዝብ መመላለሻ ትራንስፖርት በመሄድ ላይ እያሉ ዘጠኝ ታጣቂዎች መኪናውን በማስቆም እሳቸውንና አንድ ፖሊስ ለይተው በማውጣት ግለሰቡን ገድለዋቸዋል። ፖሊሱ እንዳመለጠም ተገልጿል።

ግለሰቡ ከ12 ዓመታት በላይ በፀጥታና ደህንነት ዘርፍ በተለያዩ ቦታዎች ያገለገሉ ሲሆን ቀብራቸውም ተጆ በምትባል ስፍራ ተፈፅሟል።

የታጣቂዎቹን ማንነት አስመልክቶ ቢቢሲ አቶ መሀመድን የጠየቃቸው ሲሆን የቀድሞ የኦነግ ሰራዊት አባል የነበሩና በአሁኑ ሰዓት ተበታትነው በጫካ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ደምቢዶሎ አካባቢ በምትገኘው የሰዮ ወረዳ የኦዲፒ ፅ/ቤት ኃላፊ ከአዲስ አበባ ወደ ደምቢዶሎ እየተጓዙ በነበረበት ወቅት በታጣቂዎች ተወስደው መገደላቸው የሚታወስ ነው።

በተያያዘ ዜና ደምቢዶሎ ከተማ 07 ቀበሌ አካባቢ ፖሊስ ማንነታቸውን እያጣራ ባሉ ግለሰቦች በትናንትናው ዕለት በተወረወረ ቦንብ ሁለት ሰዎች ቀላል ጉዳት ገጥሟቸዋል።