በኦሮምኛ የሥነ-ጽሁፍ እድገት ውስጥ ትልቅ መነሳሳት የፈጠሩት ኦኒስሞስ ነሲብ

ኦኒስሞስ ነሲብ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በኦሮምኛ የሥነ-ጽሁፍ እድገት ውስጥ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ይላሉ በእሳቸው ሥራዎች ላይ በርካታ ጥናት ያደረጉ ምሁራን።

መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ኦሮምኛ የተረጎሙ የመጀመሪያው ሰውም ናቸው። የቢቢሲ ባልደረቦች ወደ ትውልድ ቀያቸው ኢሉአባ ቦራ አቅንተው ዘመዶቻቸውን አነጋግረዋቸዋል።

አቶ ሽፈራው ጉደታ የኦኒስሞስ ነሲብ ዘመድ ናቸው። ስለኦኖሲሞስ ማውራት ከመጀመራቸው በፊት ስለ ነገዳቸው በማስረዳት ይጀምራሉ።

''የነገዱ ስም ሂካ አዋጂ ዋራጎ ይባላል። ይህ ነገድ በሦስት ነገሮች ይታወቃል፤ በግብርና፣ በከብት እርባታ እና በውጊያ'' ይላሉ አቶ ሽፈራው ጉደታ።

ሂካ አዋጂ ወይም አባ ገመቺስ ከኦጌ ተራራ ስር በሚገኘው በአረንጓዴያማው መንደር አራት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ኖረዋል።

''አና እና ሂካ አዋጂ አንድ ደም እና አንድ ሥጋ ናቸው'' ይላሉ አቶ ሽፈራው።

''እኔ ሽፈራው ጉደታ ኖጎ ሰርቦ ኮሮሶ ኢሬሶ እባላለሁ። አባ ገመቺስ (ኦኒስሞስ ነሲብ) ደግሞ ሂካ አዋጂ ኢሬሶ ይባላል። ስለዚህ አንድ የዘር ሃረግ ነው ያለን'' በማለት አቶ ሽፈራው ከኦኒስሞስ ነሲብ ጋር ያላቸውን ዝምድና ይናገራሉ።

አቶ ሽፈራው ሂካ አዋጂን በተመለከተ ከአያት እና ቅድመ አያቶቻቸው ሲሰሙት ያደጉትን ታሪክ ሲተርኩ ''ሂካ አዋጂ የተወለዱት 1850ዎቹ ሰፊ ጦርነቶች ይካሄዱበት የነበረበት ዘመን ነበር"

የሦስት ልጆች አባት የነበሩት የኦኒስሞስ ነሲብ አባት አቶ አዋጂ ኢሬሶ በጦር ሜዳ ላይ እያሉ ሞቱ።

የኦኒስሞስ ነሲብ እናት ወ/ሮ ሮቤ ሦስት ልጆቿን ብቻዋን ማስደግ ጀመረች።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ልጆቿን ስታሳድግ የቆየችው ወ/ሮ ሮቤ አንድ ምሽት ላይ ሦስት ልጇቿን አስከትላ ስትጓዝ አንድ ሰው ጫካ ውስጥ ጠብቆ ሂካ አዋጂን (ኦኒስሞስ ነሲብን) ነጠቃት።

እናትም በቀላሉ ልጇን አሳልፋ አልሰጠችም። የሰዎችን እርዳታ ፈልጋ ብትጮህም የደረሰላት ግን አልነበረም። ''ልጇን ይዛ አልለቅ ብትለው፤ ሰውዬው ልጁን እንደሚገድልባት አስፈራራት፤ ከዚያም 'ልጄን ከምትገድል በህይወት እንዳለ ውሰደው' አለችው'' በማለት አቶ ሽፈራው ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ ከብዙ ፍለጋ እና መንከራተት በኋላ ሮቤ ልጇ ሂካ አዋጂ ያለበትን ቦታ ማወቅ ቻለች።

''እባክህ ጌታዬ ይሄን ልጄን ትሸጠዋለህ ወይስ ባሪያ አድርገህ ታቆየዋለህ'' ስትል ልጇን የነጠቃትን ሰው ጠየቀችው ይላሉ አቶ ሽፈራው።

አቶ ሽፈራው በተነገራቸው ታሪክ መሰረት፤ ኦኒስሞስ ነሲብ በግዴታ ከተወሰደ ወዲህ ነጣቂውን እያለቀሰ ያስቸግር ስለነበረና ሊጠፋ ይችላል የሚል ስጋት ስለነበረው ልጁን ለመሸጥ ወሰነ ይላሉ።

እናት ሮቤም ''ለመሸጥ ከወሰንክ ከብቶቼን ሽጬ እስክመለስ ድረስ ሳትሸጠው ጠብቀኝ'' ብላ ወደ መንደሯ ተመለሰች።

ሮቤ በግፍ የተነጠቀውን ልጇን መልሳ ለመግዛት ያደረገችው ጥረት አልተሳካም። በአራት ዓመቱ ከእናቱ ጉያ የተነጠቀው ህጻን በባሪያ ንግድ ደላሎች ከሦስት ጊዜ በላይ ተሽጧል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በአፈ ታሪክ ሰማን እንደሚሉት ኦኒስሞስ ነሲብን የገዛው ስዊዲናዊ ትምህርት ቤት አስገብቶታል።

በልጅነቱ ለባሪያ ንግድ የቀረበው ሂካ አዋጂ (ኦኒስሞስ ነሲብ) በአዋቂነት ዘመኑ ጠንካራ እምነት ያለው ጸሃፊ እና መምህር ሆኗል።

'Making Citizens in Africa: Ethnicity, Gender, and National Identity in Ethiopia' መጽሃፍ ጸሃፊ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ላህራ ስሚዝ በኦሮምኛ የሥነ-ጽሁፍ እድገት ውስጥ ትልቅ መነሳሳት የተፈጠረው በ19ኛው ክፍለ ዘመን ኦኒስሞስ ነሲብ እና አስቴር ገኖ በመፈጠራቸው ነው ሲሉ ጽፈዋል።

ፕሮፌሰር መኩሪያ ቡልቻ በኦሮሞ ሥነ-ጽሁፍ ውስጥ የኦኒስሞስ ነሲብ አስተዋጽኦን በተመለከተ በጻፉት መጽሃፍ፤ ኦኒስሞስ ነሲብ በልጅነቱ እውቀት ለመገብየት የነበረው ፍላጎት እጅጉን ከፍ ያለ እንደነበረ አስፍረዋል።

ፕሮፌሰር መኩሪያ ኦኒስሞስ ሃይማኖት፣ ታሪክ፣ ጂኦግራፊ፣ ሂሳብ እና ቋንቋን ማጥናቱን ጽፈዋል።

ራሱን ''የኦሮሞዎች ሃገር ሰው'' እያለ ይጠራ የነበረው ሂካ አዋጂ ወይም ኦኒስሞስ ነሲብ፤ በርካታ ሃይማኖታዊ እና ሃይማኖታዊ ያልሆኑ መጽሃፎችን ጽፏል።