ሲሪላንካ የሞት ፍርድን ለማስፈፀም ከአርባ ሶስት አመታት በኋላ ሁለት አናቂዎች ቀጠረች

ሲሪላንካ ከአርባ ሶስት አመት በኋላ አራት ሰዎችን በሞት ልትቀጣ ዝግጅት ላይ ስትሆን ይህንንም ተግባር እንዲያከናውኑ ሁለት አናቂዎችን ቀጥራለች።

የኃገሪቱ ፕሬዚዳንት ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተገናኘ የታሰሩ አራት ግለሰቦች ላይ የሞት ፍርድ መወሰናቸውን ካወጁ በኋላ ነው ሁለቱ ሰዎች የተፈለጉት።

በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 1976 ተቋርጦ የነበረው የሞት ቅጣትም በነዚህ ግለሰቦችም ይጀመራል ተብሏል።

የሁለቱ አናቂዎች የስራ ማስታወቂያ የወጣው በየካቲት ወር ሲሆን ተፈላጊዎች ተግባሩን ለማከናወን ማሟላት ካለባቸውም መስፈርቶች መካከል "ጠንካራ የግብረገብ ባሕርይን የተጎናፀፉ፣ ዕድሜያቸው ከ18-45 የሚሆን፣ ወንድና "የአዕምሮ ጥንካሬ" የሚሉ ይገኙታል።

የኃገሪቱ ሚዲያ ዴይሊ ኒውስ እንደዘገበው ከመቶ በላይ ሰዎች ለስራው ያመለከቱ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ሁለት ሴቶች እንዲሁም ሁለት አሜሪካውያን ይገኙበታል።

የእስር ቤቶች ቃል አቀባይ እንደተናገሩት የተመረጡት ሁለቱ አናቂዎች የመጨረሻ ስልጠና መውሰድ የሚጠብቃቸው ሲሆን ይህም ሁለት ሳምንታትን ይፈጃል ተብሏል።

የመጨረሻው አናቂ የማነቂያውን ስፍራ ሲመለከት በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ተዘፍቆ ከአምስት አመታት በፊት የለቀቀ ሲሆን ሌላ አናቂ ከአመት በፊት ቢቀጠርም ስራው ቦታ ሳይመጣ ቀርቷል።

በሲሪላንካ መድፈር፣ አደንዛዥ እፅ ማዘዋወርና ነፍስ ማጥፋት በህጉ መሰረት የሞት ቅጣት የሚያስቀጡ ቢሆንም ከጎርጎሳውያኑ 1976 ጀምሮ ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቷል።

ፕሬዚዳንት ማይትሪፓላ ሲርሴና እንደገለፁት የሞት ፍርድን እንደገና ማምጣት ያስፈለገው በሃገሪቷ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ የመጣውን የአንደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ለመቆጣጠር ነው።

የፖለቲካ ተንታኞች በበበኩላቸው በዚህ አመት መጨረሻ ለሚደረገው ምርጫ ያላቸውን ተቀባይነት ለመጨመር ነው ይላሉ።

"አራት ግለሰቦች በሞት እንዲቀጡ የሚያስተላልፈውን ውሳኔ ፈርሜያለሁ" በማለት የተናገሩት ፕሬዚዳንት ሲርሴና "እስካሁን ድረስ ግለሰቦቹ የሞት ቅጣት ተፈፃሚ እንደሚደረግባቸው አልተነገራቸውም፤ የግለሰቦቹን ማንነት በአሁኑ ሰዓት መግለፅ የማንፈልገው በእስር ቤቶች ውስጥ ሊነሳ የሚችለውን መበጣበጥ ለማስቀረት ነው" ብለዋል

ፕሬዚዳንቱ እንደሚሉት በሃገሪቷ ውስጥ 200 ሺ ግለሰቦች በአደንዛዥ ዕፅ ሱስ የተጠቁ ሲሆን፤ በሃገሪቷ ካሉ እስር ቤቶች ውስጥ 60%ቱ እስረኞች ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ ክስ ነው።

ይህ ውሳኔያቸው በብዙዎች ዘንድ 'ኢሰብአዊ ድርጊት' ነው እየተባለ በመኮነን ላይ ሲሆን ሲሪላንካውያንም ውሳኔውን አደባባይ በመውጣት ተቃውመውታል።

እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ኖርዌይን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረት የሞት ፍርድን እንደገና የማምጣት ውሳኔዋን አውግዘውታል።