በዱባይ በደረሰ የመኪና አደጋ 17 ሰዎች ሞቱ

በዱባይ 31 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ አውቶቡስ ከመንገድ ምልክት ጋር በመጋጨቱ በደረሰ አደጋ የ17 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በርካቶች ለጉዳት ተዳርገዋል። ሟቾቹ የተለያየ አገራት ዜጎች እንደሆኑም ታውቋል።

መለያ ቁጥሩ በኦማን የተመዘገበው ተሽከርካሪው አደጋ ሲደርስበት 31 ሰዎችን አሳፍሮ በሸክ መሐመድ ዛይድ ጎዳና ላይ እየተጓዘ እንደነበር ፖሊስ አስታውቋል።

ከሟቾቹ መካከልም ስምንቱ የሕንድ ዜጎች መሆናቸውን የሕንድ ባለሥልጣናት አረጋግጠናል ብለዋል።

በዱባይ የሚገኘው የሕንድ ኤምባሲ የሟቾቹን ሕንዳውያን ስም ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲሆን ለቤተሰቦቻቸውም አሳውቀዋል፤ ሌሎች ጉዳት የደረሰባቸው ሕንዳውያንም ህክምና እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።

የ50 ዓመቱ የአውቶብሱ አሽከርካሪ ቀላል ጉዳት ያጋጠመው ሲሆን ሕክምና እየተደረገለት ይገኛል።

የዱባይ ፖሊስ በይፋዊ የትዊተር ገፁ ላይ በተፈጠረው አደጋ ማዘኑንና ለተጎጅ ቤተሰቦችም መፅናናትን እንደሚመኝ አስፍሯል።

የፖሊስ ኃላፊው ማጅ አብዱላህ ካሊፋ አል ማሪ "አንዳንድ ጊዜ ተራ ስህተት አሊያም ግድ የለሽነት እንዲህ ዓይነት አስከፊ አደጋዎችን ያስከትላሉ" ብለዋል።

የአደጋው ምክንያት እየተጣራ ሲሆን ስለ አደጋው ዝርዝር ሁኔታ የተባለ ነገር የለም። ይሁን እንጂ አሽከርካሪው የመንገድ ምልክትን በመጣሱ በድንገት መንገድ ለመቀየር ሲል አደጋው እንዳጋጠመው የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የኦማን የአውቶቡስ አምራች ምዋሳላት " በአደጋው የተሰማቸውን ሃዘን የገለፁ ሲሆን ከሙስካት ዱባይ የሚሰጡትን አገልግሎት ለጊዜው ማቋረጣቸውን አስታውቀዋል።