ኔይማር የቀረበበትን ወሲባዊ ትንኮሳ ክስ አጣጣለ

ብራዚላዊው ዕውቅ እግር ኳሰኛ ኔይማር በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ በአንዲት ሴት ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ አድርሰሃል ተብሎ ክስ ቀረበበት።

በሳኦ ፖሎ ብራዚል የተመሰረተበት የክስ ሪፖርት እንደሚያሳየው ከሆነ፤ ከሳሿ ሴት ኔይማር በሚጫወትበት ፓሪስ መሃል ከተማ በሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ ወሲባዊ ትንኮሳውን ፈጽሞብኛል ብላለች።

የቀረበውን ክስ በማስመልከት የኔይማርም ወኪሎች ''ሙሉ በሙሉ የተሳሳተ'' ሲሉ አሳጥለውታል።

ኔይማር በአሁኑ ሰዓት ለኮፓ አሜሪካ ውድድር ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር በብራዚል ልምምድ እያደረገ ይገኛል።

የቀረበበት ክስ ምንድነው?

የፖሊስ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ከሳሿ ኔይማርን የምታውቀው ኢንስታግራም ላይ ሲሆን፤ ኔይማር ፓሪስ ከተማ እንዲገናኙ እንደጠየቃት ቃሏን ሰጥታለች።

ከዚያም ከብራዚል ፈረንሳይ የአየር ቲኬት እንደገዛላት እና ሆቴል ሶፊትል ፓሪስ አርክ ዲ ቲሪየምፍ በተሰኘ ቅንጡ ሆቴል እንድታርፍ እንዳደረገ ጨምራ ለፖሊስ ተናግራለች።

ኔይማርም ወደተጠቀሰው ሆቴል ግንቦት 7 ሲመጣ ''በግልጽ ሰክሮ'' ነበር ትላለች። ለጥቂት ደቂቃዎች ከተነጋገሩ በኋላ ኔይማር ይህቺን ሴት ወደ ራሱ አስጠግቶ በመያዝ ''ያለሴቲቱ ፍቃድ በኃይል ወሲብ ፈጽሟል'' ይላል የፖሊስ የክስ መዝገብ።

ከዚያም ጥቃቱ የተፈጸመባት ሴት ከሁለት ቀናት በኋላ የደረሰባትን ጥቃት ለፈረንሳይ ፖሊስ ሳታሳውቅ ወደ ብራዚል ተመለሰች። "በደረሰባት ጥቃት እጅጉን ተደናግጣ እና ፈርታ ስለነበረ በሌላ ሃገር የደረሰባትን እውነታ ማሳወቅ አልተቻላትም'' ይላል ለፈረንሳይ ፖሊስ ለምን ሪፖርት እንዳላደረገች የክስ ሪፖርቱ ሲገልፅ።

የኔይማር አባት ምን ይላሉ?

የእግር ኳሰኛው አባት፣ ኔይማር ዶስ ሳንቶስ፣ ቅዳሜ ዕለት ለብራዚል ቴሌቪዝን ሲናገሩ ''ይህ ግልጽ የሆነ ወጥመድ ነው።'' ብለዋል።

''በጉዳዩ ላይ የሕዝብ አመለካከት ካልጠራ እና እውነታውን በፍጥነት ማሳየት የማንችል ከሆነ፤ ይህ ጉዳይ እየተባባሰ ነው የሚሄደው። ኔይማር ከዚህች ሴት ጋር በዋትስአፕ ያደረጋቸውን ግንኙነቶች ብንመለከት እውነታው ይታወቃል'' ይላሉ የኔይማር አባት።

የ27 ዓመቱ አጥቂ የሥነምግባር ጉድለት የብራዚል ብሔራዊ ቡድን አምበልነትን አሳጥቶታል።

ከአንድ ወር በፊት ክለቡ ፒኤስጊ በሌላ ክለብ መሸነፉን ተከትሎ ኔይማር ደጋፊን በመማታቱ የፈረንሳይ የእግር ኳስ ኃላፊዎች በሦስት ጨዋታዎች ላይ እንዳይሰለፍ ውሳኔ አስተላልፈውበታል።

ኮፓ አሜሪካ የደቡብ አሜሪካ ሃገራት ውድድር ሲሆን ከ12 ቀናት በኋላ በአዘጋጇ ሃገር ብራዚል ይከናወናል።