ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ 6 ዋና ዋና ዕቅዶች
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ከፍተኛው የሃገሪቱ የስልጣን መንበር የመጡበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው የሚሌኒየም አዳራሽ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ባለፉት አስራ ሁለት ወራት በመንግሥታቸው ስለተከናወኑት ተግባራትና ስላጋጠሙት ተግዳሮቶች ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጠቀሷቸው የመንግሥታቸው ስኬቶች መካከል ባለፉት 100 ዓመታት በአንድ ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያ አግኝታ የማታውቀውን የውጪ ምንዛሬ መጠን በ7 ወራት ውስጥ 13 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት እንደቻለችና በዚህ ጊዜም 8 ቢሊዮን ዶላር ለግሉ ዘርፍ መቅረቡን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱት መፈናቀሎች ካጋጠሙ ችግሮች ውስጥ በቀዳሚነት ጠቅሰው በፖለቲካ ኃይሎች መካከል ያለው መጠላለፍ ሃገሪቱ እያካሄደች ላለው ለውጥ እንቅፋት እንደሆነም ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ የስልጣን ዘመናቸው ኢትዮጵያዊያን ከዳር እስከ ዳር በጋራ በመቆም በማይግባቡበት እየተወያዩ ኢትዮጵያዊነትን የሚያደምቁበት ዓመት እንዲሆን ጥሪ አቅርበው፤ በቀጣይነት መንግሥታቸው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራባቸውን ጉዳዮች በዝርዝር አስቀምጠዋል።
- የተጀመሩት ተቋማዊ ለውጦች ሁሉን አሟልተው ተግባራዊ እንዲሆኑ በማድረግ የተጀመረውን ተቋማዊ ለውጥ አጠናክሮ ገለልተኛ፣ ነጻና ሁሉን ኢትዮጵያዊ በእኩል የሚያገለግሉ ተቋማት መገንባት የዕቅዳቸው ቀዳሚ አካል ነው።
የሕግ የበላይነትን በተመለከተ ሁሉም ሕግ የሚያስከብሩና ሕግ የሚተረጉሙ አካላት ከተሻሻሉት ሕጎች በተጨማሪ እያንዳንዱን ዜጋ ከጥቃት የሚከላከሉ ሃቀኛ ፍትህን ከፍርድ ቤቶች የሚያስገኙ ሥራዎች በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲያቆሙ ማድረግም የዕቅዳቸው አካል አድርገው ጠቅሰዋል።
2. የሥራ ዕድል ፈጠራ ሌላኛው በቀጣይ አንድ ዓመት ሊያሳኩ ካቀዱት መካከል ይገኛል። ገለልተኛ ተቋማትና ጠንካራ መንግሥትን በመገንባት የውጪ ባለሀብቶች በተለያዩ መስኮች እንዲሰማሩ በማድረግ ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ማድረግ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠውም ተናግረዋል። እንዲሁም የማዕድን ዘርፍን ማጎልበትና የውጪ ምንዛሪን ማስገኘት ከዕቅዳቸው መካከል ይገኝበታል።
3. የተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይም ሌላኛው ዕቅዳቸው ነው። እነዚህ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደነበሩባቸው ቦታ እንዲመለሱ ማድረግ ብቻ ሳይሆን እንዲቋቋሙ መንግሥት ከሕዝቡ ጋር በመሆን እንደሚሰራ ተናግረዋል።
4. በግብርናው ዘርፍ በዚህ ዓመት በትናንሽና በመካከለኛ የመስኖ ሥራ ላይ የተጀመሩት ሥራዎችና ጥናቶችን አጠናክሮ ፍሬያማ ለማድረግም አልመዋል።
5. በቱሪዝም መስክ በመጪው መስከረም ወር የብሔራዊ ቤተ መንግሥት ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚደረግና የአዲስ አበባን ገጽታ ለመቀየር እየተሰራ ያለው ፕሮጀክትም በመጪው ዓመት አንድ አራተኛው ተጠናቆ ክፍት እንደሚሆን ተናግረዋል።
6. በሚቀጥለው ዓመት በምርጫ ቦርድ ውሳኔ መሰረት የሚኖረው ምርጫ ፍጹም ነጻና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲከናወን በማድረግ በአፍሪካ ደረጃ አርዓያ እንዲሆን ይሰራልም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ አንድ ዓመት ውስጥ መንግሥታቸው ሊሰራ ያቀዳቸውን ጉዳዮች ካስቀመጡ በኋላ ባለፈው አንድ ዓመት ሕዝቡ እየጠበቀ የጎደለና ያልተሟላ ነገር ካለ ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቀዋል።
ሕዝቡ ተስፋ አድርጎ በአስተዳደራቸው በኩል ያልተፈጸሙ ነገሮች ካሉ በዳተኝነትና በንዝህላልነት ሳይሆን ምናልባት ከዕውቀት ማነስና ከሁኔታዎች አለመመቸት እንደሚሆን ተናግረው፤ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው የተጣለባቸውን ኃላፊነት ሲወጡ እንደቆዩ ተናግረዋል።