ለኤችአይቪ መድሃኒት ሊገኝለት ይሆን?

ለ16 ዓመታት የኤችአይቪ ተጠቂ የነበረ በሀገረ እንግሊዝ የሚኖር አንድ ግለሰብ ከረዥም የሙከራ ህክምና በኋላ ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ ተሰምቷል።

የካንሰር በሽታም ተጠቂ የሆነው የለንደን ከተማ ነዋሪ የሙከራ ህክምናውን ለ18 ወራት ሲከታተል የነበረ ሲሆን በሰውነቱ ውስጥ ያለው ደም ከቫይረሱ ነጻ ስለሆነ የኤችአይቪ መድሃኒቶቹን መውሰድ አቁሟል።

ተመራማሪዎቹ እነደሚሉት ግን ሙሉ በሙሉ ከቫይረሱ ተፈውሷል ለማት ጊዜው ገና ነው ብለዋል።

የዘርፉ ባለሙያዎች በህክምናው ውጤት መደመማቸውን ቢገልጹም ተመራማሪዎቹ ቫይረሱን ከደም ውስጥ ለማጥፋት የተጠቀሙት መንገድ ሁሉም ተጠቂዎች ላይ ተግባራዊ መሆን የሚችል ባለመሆኑ ተጨማሪ ስራ ይጠይቃል ብለዋል።

ለወደፊቱም ለቫይረሱ ፈውስ ለማግኘት ትልቅ መነሻ ሊሆን እንደሚችልና ለብዙ ዓመታት ሲጨነቁ ለነበሩ ተጠቂዎች ተስፋ ሰጪ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

በሙከራ ህክምናው ላይ የለንደን ኮሌጅ ዩኒቨርሲቲ፣ የለንደን ኢምፔሪያል ዩኒቨርሲቲ፣ የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲና የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማዎች ተሳትፎ ማድረጋቸው ታውቋል።

በዚህ አይነት መንገድ ቫይረሱን ከደም ውስጥ የማጥፋት ስራ ሲከናወን ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

የዛሬ አስር ዓመት አንድ ጀርመናዊ የቫይረሱ ተጠቂ ተፈጥሮአዊ የመከላከል ብቃት ካለው በጎ ፈቃደኛ በተገኘ የመቅኔ (ቦን ማሮው) ንቅለ ተከላ ተደርጎለት ነጻ መሆን መቻሉ ይታወሳል።

ምንም እንኳን ይሄኛው ግኝት አስደሳች ቢሆንም በሚሊዮን ለሚቆጠሩት የዓለማችን የኤች አይቪ ተጠቂዎች ተደራሽነቱ አጠራጣሪ ነው። የህክምና ሙከራው ከሌሎቹ ለየት ባለ መልኩ ለካንሰር ህክምና የሚደረጉ ስርአቶችን ይከተላል።

አሁን ያሉት የኤችአይቪ ማዳከሚያ መድሃኒቶች ተጠቂዎቹ ጤናማና ረጅም እድሜ እንዲኖሩ የሚያስችሏቸው ስለሆኑ ይሄኛውን መንገድ እንደ ብቸና አማራጭ አድርጎ ለመወሰድ ከበድ ያደርገዋል።

ሰውነታችን እራሱን ከበሽታ እንዴት እንደሚከላከል በእርግጠኝት ለመረዳትና ለወደፊት ፍቱን መድሃኒቶችን ለማግኘት ግን ይሄኛው ህክምና ፈር ቀዳጅ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

በለንደን ኢምፔሪያል ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑትና በጥናቱ የተሳተፉት ፕሮፌሰር ኤድዋርዶ ኦሊቬራ እንደሚገልጹት በህክምናው ሂደት ''ሊምፎማ' የተሰኘውን የካንሰር አይነት ለማከም የሚጠቀሙበትን መንገድ ተግባራዊ ስላደረጉ ሂደቱን አስቸጋሪ ያደርገዋል።

''የህክምና መንገዱ በራሱ መርዛማ የሆኑ ነገሮችን ስለሚያካትትና ለረዥም ጊዜ ስለሚካሄድ ተግባራዊነቱን ትያቄ ውስጥ ይከተዋል። ነገር ግን ወዴት መሄድ እንዳለብን ትክለኛ አቅጣጫ ጠቋሚ ነው።''