ከእንጀሯ አባቷ ያረገዘችውን ፅንስ ልታቋርጥ ሞክራለች የተባለችው ሴት ነፃ ሆና ተገኘች

በውርጃ ምክንያት የተከሰሰችው ሴት ነፃ ሆነች

የፎቶው ባለመብት, REUTERS

ኤል ሳልቫዶራዊቷ ሴት የሃገሪቱን ጥብቅ የፀረ-ውርጃ ሕግ ጥሳለች በሚል ምክንያት ተፈርዶባት የነበረው እሥር እንዲነሳላት የሃገሪቱ ፍርድ ቤት ወሰነ።

ኢሜልዳ ኮርቴዝ የተሰኘችው የ20 ዓመት ወጣት ሴት ብዙ ወሲባዊ በደል በሚያደርስባት እንጀራ አባቷ ተደፍራ ነው ያረገዘችው።

መፀዳጃ ቤት ውስጥ ሴት ልጅ ከመገላገሏ በፊት ውርጃ ለማካሄድ ሞክራለች ሲሉ ነው ዶክተሮች ኢሜልዳን የከሰሷት።

ሴት ልጇ በመልካም ደህንነት ብትገኝም ኢሜልዳ በፖሊስ ተይዛ ፍርዷን እየተከታተለች ለ18 ወራት ያክል እሥር ቤት ከረመች።

አቃቤ ሕግ ሴቲቱ ስለእርግዝናዋ ለማንም አለመናገሯ፤ ሕክምና አለመከታተሏ እና ውርጃ ለመፈፀም መሞከሯ እስከ 20 ዓመት እሥር የሚያደርስ ጥፋት ነው ሲል ተከራክሯል።

ሰኞ ዕለት ችሎት የዋለው የሃገሪቱ ፍርድ ቤት ግን ኢሜልዳ በእንጀሯ አባቷ በተደጋጋሚ በመደፈሯ ምክንያት ነፍሰ-ጡር መሆኗን ሳታውቅ ነው የወለደችው በሚል ነፃ እንድትሆን በይኗል።

ጠበቃዎቿ ቀለል ያለ ቅጣት መቀጣት ካለባትም ልጇን ችላ በማለቷ ለአንድ ዓመት ልትቀጣ ይገባል እንጂ 20 ዓመት አይገባትም በማለት ተከራክረው ነበር።

ፍርድ ቤቱ ግን ምንም ዓይነት ወንጀል ባለመፈፀሟ ነፃ ናት ሲል ለሃገሪቱ ህዝብ ጆሮ አዲስ እና አስደሳች የሆነ ብይን አሰምቷል።

ኢሜልዳ ነፃ መሆኗን የሰሙ ወዳጅ ዘመዶቿ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ሰዎች መፈክር በመያዝ ፍርድ ቤቱን አጥለቅልቀውት ታይተዋል።

አቃቤ ሕግ የ70 ዓመቱ አባቷ በቁጥጥር ሥር ውሎ ፍርዱን እየተከታተለ እንደሆነ አሳውቋል።

ኤል-ሳልቫዶር ዓለማችን ላይ ጠንካራ ፀረ-ውርጃ ሕግ ካላቸው ጥቂት ሃገራት አንዷ ነች፤ ምንም ዓይነት የውርጃ ድርጊት ለእሥር ይዳርጋል።

ውርጃ ለመፈፀም የሞከሩ ሴቶች ብቻ ሳይሆኑ ድርጊቱን እያወቁ የደበቁ የሕክምና ባለሙያዎችም ከበድ ያለ እሥር ሊጠብቃቸው ይችላል።