ብሄራዊ ባንክ ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ጋር የግሉን ዘርፍ ለማገዝ ስምምነቶችን አደረገ

የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስኪያጅ ፍሊፕ ለ ዌሩ በኢትዮጵያ በነበራቸው የስድስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ወቅት ብሄራዊ ባንክ ከኮርፖሬሹ ጋር የግሉን ዘርፍ ለማገዝ ስምምነቶችን አደረገ ነው።
የመጀመሪያው ስምምነት ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ለተመረጡ የኢትዮጵያ ባንኮች በዓለም አቀፍ የንግድ ፋይናንስ መርኃ ግብር አማካይነት ድጋፍ የሚያደርግበት ሲሆን ሁለተኛው ስምምነት ደግሞ ኮርፖሬሽኑ ለኢትዮጵያ በብር ብድር የሚያቀርብበት ነው ተብሏል።
"የዛሬው ስምምነት ኢትዮጵያ ለግሉ ዘርፍ ዕድገት ያላትን ቁርጠኛነት ይጠቁማል" ሲሉ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የተናገሩት የፋይናንስ እና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ናቸው።አቶ አህመድ ጨምረውም መንግሥት የፋይናንስ ዘርፉን ለማሳደግ ከፖሊሲ ምርመራ አንስቶ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል። የብሄራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ በበኩላቸው ስምምነቶቹ ኢትዮጵያ ላጋጠማት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግር የመፍትሄ አካል ከመሆኑም በላይ ለግሉ ዘርፍ ፋይናንስ በማቅረብ ረገድ ከፍ ያለ ሚና አለው ብለዋል።
ለግሉ ዘርፍ የፋይናንስ ምንጩን ማብዛት አለብን፤ ይህ የዚህ ስምምነት አንደኛው አካል ነው" ብለዋል ገዥው።ከዚህም በተጨማሪ "የግሉን ዘርፍ ባካተተ ሁኔታ የካፒታል ገበያ በኢትዮጵያ አውድ እንዴት ሊሠራ እንደሚችል ጥናት እያካሄድን ነው" ሲሉ የባንኩ ገዥ አክለው ተናግረዋል።ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (አይኤፍሲ) በዓለም ባንክ ሥር የግሉን ዘርፍ የሚመለከት ክንፍ ሆኖ የተቋቋመው እ.ኤ.አ በ1950ዎቹ አጋማሽ ሲሆን በማደግ ላይ ባሉ አገራት የግሉን ዘርፍ ዕድገት የማበረታትን ሥራ ይከውናል። አይኤፍሲ አባል ሆነው በመሠረቱት አገራት ባለቤትነት የተያዘ እና የሚተዳደር ተቋም ነው።
ፈረንሳይዊው ፍሊፕ ለ ዌሩ እ.ኤ.አ ከመጋቢት 2016 አንስቶ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።ሥራ አስኪያጁ በኢትዮጵያ የስድስት ቀናት ቆይታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር የተገናኙ ሲሆን የሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክንም ጎብኝተዋል። ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች ጋር በነበራቸው ቆይታ የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ እርስ በእርስ እንዲተማመኑ እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ፍፁም አረጋ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የንግድ ሥራ ክንውን የሚያቀላጥፉ የማሻሻያ እርምጃዎችን ለመውሰድ በኮሚሽኑ እና በኮርፖሬሽኑ መካከል የትብብር ስምምነት ላይ መደረሱንም አቶ ፍፁም አክለው ገልፀዋል።ሥራ አስጂያጁ በልጅነታቸው ወቅት አዲስ አበባ በሚገኘው የሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከተታትለው የነበረ ሲሆን በቆይታችው ወቅት ትምህርት ቤቱን እንደጎበኙ ዛሬ ሰኞ ቀትር ላይ ለጋዜጠኞች ባደረጉት ገለፃ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ባንኮች ከተለያዩ የዓለም አገራት ባንኮች ጋር የብድር ስራን በሚያከናውኑበት ወቅቅ በቂ የሆነ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ካልተገኘ በስራው ላይ ችግሮች እንደሚፈጠሩ ያስረዱት የብሄራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ፤ የዛሬው ስምምነት አይኤፍሲ ዋስትና እንደሚሰጥ የሚያረጋግጥ በመሆኑ፤ ይህም የኢትዮጵያ ባንኮች ከውጭ አገራት አቻዎቻቸው ጋር ያላቸውን ስራ የሚያቀል ነው ብለዋል። "ሲጠቃለሉ ሁለቱ ስምምነቶች ተጨማሪ ዶላር ላገሪቱ ያስገኛሉ፤ ለግሉ ዘርፍ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ያመጣል፤ ላገጠመን የውጭ ምንዛሬ ችግር ዋስትና ይሰጣል" ሲሉ ተናግረዋል።












