በአሜሪካ በረራ ላይ ሴት የተነኮሰው ህንዳዊ ዘብጥያ ወረደ

የአሜሪካ ፍርድ ቤት በአሜሪካ በረራ ላይ አጠገቡ ተቀምጣ የነበረችውን ግለሰብ የተነኮሰውን ህንዳዊ የዘጠኝ አመት እስር ፈርዶበታል።

ትንኮሳ የተፈፀመባት ግለሰብ በበረራው ወቅት ብራብሁ ራማሞርቲ ከተሰኘው ግለሰብና ባለቤቱ መሀል ተቀምጣ ነበር።

በወቅቱ ተኝታ የነበረ ሲሆን ድንገት ከእንቅልፏ ብንን ስትል የሸሚዟ ቁልፍና የሱሪዋ ዚፕ ተፈትቶ የግለሰቡን እጅ ሱሪዋ ውስጥ አግኝታዋለች።

ይህ የ34 ዓመቱ ግለሰብ እስሩን ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ህንድ ተጠርዞ እንደሚላክ ፍርድ ቤቱ በተጨማሪ አስታውቋል።

አቃቤ ህግ 11 ዓመት እንዲፈረድበት ጠይቆ የነበረ ቢሆንም "ምንም እንኳን ወንጀሉ ከፍተኛ ቢሆንም" ዘጠኝ አመት በቂ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ መወሰኑን የዲትሮይት ፍሪ ፕሬስ አስታውቋል።

ግለሰቡም በበኩሉ በወቅቱ ተኝቶ እንደነበር በመግለፅ ወንጀሉን ክዷል።

በተያዘበት ወቅትም አቃቤ ህግ ሊያመልጥ ይችላል የሚል መከራከሪያ በማንሳቱ የዋስ መብቱን ተከልክሎ ነበር።

ጥቃት የደረሰባት ግለሰብ ለአውሮፕላኑ አስተናጋጆች ምን እንደደረሰባትም ሪፖርት አድርጋለች።

የግለሰቡ ባለቤት በበኩሏ ሴትዮዋ ጉልበቱ ላይ ተኝታ ነበር ስትል የወነጀለቻት ሲሆን፤ ሴትዮዋ ሌላ መቀመጫ እንዲሰጣት መጠየቋንም ገልፃለች።

ነገር ግን የበረራው አስተናጋጆች በበኩላቸው ጥቃት የደረሰባት ግለሰብ ብቻ እንዲቀይሯት የጠየቀች ሲሆን ፤ የግለሰቡ ባለቤት የተናገረችው ሀሰተኛ እንደሆነ ለመርማሪዎች ተናግረዋል።

በወቅቱም እያለቀሰች የነበረ መሆኑን ገልፀው የሸሚዟም ሆነ የሱሪዋ ቁልፎች ተፈትተው እንደነበር አስተናጋጆች ጨምረው ለመርማሪዎች አስረድተዋል።

ከኋላ ወንበር ፈልገው እንዳስቀመጧትም አክለዋል።