ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቄሮ፣ ሴታዊት፣ ፋኖ…የትውልዱ ድምጾች
እያንዳንዱ ትውልድ የራሱ ድምፅ አለው እንደሚባለው በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይም ይሁን መሬት ላይ ተፅእኖ እየፈጠሩ ያሉ እንቅስቃሴዎች አሉ። የመንግሥታዊ ሥርዓት ለውጥን ከማምጣት ጀምሮ በማህበረሰቡ የማይደፈሩ ሃሳቦችን የሚያነሱ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተፈጥረዋል። ከነዚህም ውስጥ ቄሮ፣ ፋኖ፣ ዘርማ፣ ሴታዊትና የሎው ሙቭመንት ይገኙበታል።
ሴታዊት "አልነካም ባይ ሴት"
በዓመቱ መጨረሻ በጳጉሜን ወር #የጳጉሜ ንቅናቄ በሚል በአምስቱ ቀናት ውስጥ በማህበራዊ ሚዲያ ብዙዎችን ያሳትፈ ዘመቻ ነበር።
እህትማማችነት፣ አሪፍ ወንድ፣ የሴቶች የሥነ-ተዋልዶና ወሲባዊ ጤንነት፣ ሴቶችና የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲሁም በቅርቡ ጾታዊ ጥቃት ተፈጽሞባት ህይወቷን ያጣችው ጫልቱን የሚዝክር 'ለጫልቱ የምንገባላት ቃል' በሚሉ ርዕሶች ላይ ብዙዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
ከእነዚህ ዘመቻዎች ጀርባ የፆታ እኩልነት ጥያቄዎችን፣ አባታዊ ሥርዓትን እና የፆታ አስላለፍ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ሙግቶችን በማንሳትና ውይይቶችን በመፍጠር የምትታወቀው ሴታዊት ናት።
እንቅስቃሴዋ የተጀመረችው ከአራት ዓመታት በፊት 'ፌሚኒስት' የሆኑና በፆታ እኩልነት በሚያምኑ ሴቶች በወር አንድ ጊዜ በመገናኝት ነበር።
ከወንዶችና ከሴቶችም እንቅስቃሴውን የመቀላቀል ጥያቄ ሲነሳ "ኦፕን ሴሺን" ተብሎ የሚጠራውና ለሁሉም ክፍት የሆነውን ዝግጅት በሦስት ወር አንድ ጊዜ ማዘጋጀት ጀመሩ። በእነዚህ ዝግጅቶች ላይ የህትመት ውጤቶችን ያበረከቱ ፀሀፍት ወይም ተመራማሪዎች ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ።
በሚቀጥለው ዓመትም በቅርቡ ተደፍራ ህይወቷን ያጣችው ጫልቱን ማን ገደላት? በሚል ርዕስ ዘመቻ ለማካሄድ አቅደዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ የፍልስፍና ጥናት፣ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ጥያቄ፣ በተለያዩ ባህሎችና የትግል እንቅስቃሴ የሴቶች ጥያቄ የተነሳበትን መንገድ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፌሚኒዝም እንዴት ይታያል? በሚልም ዘለግ ያለ ጥናት በማካሄድ ላይ ናቸው።
የሎው ሙቭመንት "እንደማመጥ፤ እንወያይ፤ እርስ በርስ ደግ መሆንን እናበረታታ"
ከጥቂት አመታት በፊት የበረራ አስተናጋጅ የነበረችው አበራሽ ሃይላይ በቀድሞ የህይወት አጋሯ በደረሰባት ጥቃት አይኗን ማጣት ብዙዎችን ያስደነገጠ ዜና ሲሆን አጋጣሚው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለነበሩ ጥቂት ተማሪዎች የፆታ እኩልነት ጥያቄ ያነገበውን የየሎው ሙቭመንት እንቅስቃሴ እንዲጀምሩ ምክንያት ሆነ።
መለያቸው ቢጫ ቀለም ነው። በየዓመቱ ብር እያሰባሰቡ ችግረኛ ለሆኑ ሴት ተማሪዎች ድጋፍ ማድረግ፣ በወሊድ ጊዜ ለሚቸገሩ እናቶች የደም ልግሳንና ሌሎች እርዳታዎቸንም ያስተባብራሉ።
ቄሮ "የራስን ዕድል በራስ የመወስን መብት"
ከጥቂት ዓመታት በፊት በኦሮሚያ ክልል ከተካሄዱት ተቃውሞዎች ጋር ተያይዞ የቄሮ ስም በተደጋጋሚ ይነሳል። ምንም እንኳን ቄሮ በቅርብ ዓመታት ቢታወቅም ቄሮ የሚለውን ስም ከመያዙ በፊት የኦሮሞ ወጣቶች በተለያየ መንገድ ይንቀሳቀሱ እንደነበር ገመቹ ከፈና ይናገራል።
የትግሉም አላማ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ጭቆና ማስወገድና ፍትሐዊ ሥርዓትን ለመገንባት አቅጣጫ የያዘ ትግል እንደነበረም ገመቹ ያወሳል። በዚህ ወቅት ከመንግሥትም ሆነ ከተለያዩ የፀጥታ ኃይሎች ለትግሉ የተሰጠው ምላሽ እስርና ግድያ በመሆኑ ትግሉ አቅጣጫውን እንዲቀይር እንዳደረገው ገመቹ ያመለክታል።
ቄሮ በአንድ ጊዜ የመጣ ሳይሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ የመጣ አደረጃጀት ሲሆን መነሻውም የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር ነው። ቄሮ የፍልስፍና አደረጃጀቱን ከገዳ ሥርዓት የተወሰደ ሲሆን ይህም ያላገባ ወጣትን ሁሉ እንደሚያጠቃልል ገመቹ ይናገራል።
የትግሉ አላማም የራስን ዕድል በራስ የመወስን መብት፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን እና የመሬት መቀራመትን መቃወም ላይ ያተኮረ ነው።
ምንም እንኳ ስለ ቄሮ አመሰራረትም ሆነ ስለ መሪዎቹ የተለያየ ህሳብ ቢኖርም ቄሮ መሪ አልባ ድርጅት ነው በሚለው ሀሳብ ገመቹ በፍፁም አይስማማም።
ይልቁንም የድርጅት መልክ አወቃቀርና ተቋማዊ መልክ አለው ይላል። እንደ ማሳያነት የሚጠቅሰውም ከሦስትና ከአራት ዓመታት በፊት የነበረው ትግልን በስትራቴጂ የተነደፈ መሆኑን፣ በግልፅ የሚታወቁና የህቡዕ መሪዎች ያሉት መሆኑን ነው።
"የህዝቦችን ጥያቄ በመነጋገርና በሰላም መፍታት የሚቻልበት ደረጃ የደረሰው በቄሮ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ወጣቶች ትግልም ነው" ይላል። ይህ ሁሉ ሲሆን ብዙ መስዋእትነት የተከፈለ ሲሆን ገመቹም ለስድስት ዓመት ከስምንት ወራት ያህል በእስር ቤት ቆይቷል።
ፋኖ፡ መገፋት የወለደው «የለውጥ ኃይል»
በበደል ተገፍቶ ዱርን የመረጠ፣ መጨቆንን ጠልቶ ጠመንጃ የጨበጠ ሰው «ፋኖ» ይባላል።
ከሦስት ዓመታት ወዲህ አብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል በህዝባዊ ተቃውሞ በተናጠበት ወቅት በአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች የነበሩ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን በህቡዕ ሲያስተባብር የነበረው ቡድን ስያሜም ይሄን መሰረት ያደረገ እንደሆነ ከመስራቾቹ መካከል አንዱ የሆነው የለውጥ አራማጅ ሙሉቀን ተስፋው ይናገራል።
ሙሉቀን ጋዜጠኛ ነበር። በስራ ምክንያት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚዘዋወርበት ወቅት በአማራ ተወላጆች ላይ የሚደርሰውን በደል ሲታዘብ መቆየቱን፣ የበደል እና ጭቆና ምንጭ የሆነው አገዛዝ መወገድ አለበት በሚል እምነት ከሌሎች ጓዶቹ ጋር የአማራ ወጣቶችን ለማደራጀት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ያወሳል።
«ከ2003 ዓመተ ምህረት ጀምረን በአማራ ተወላጆች ላይ ችግር ደርሷል በተባለበት ቦታ ሁሉ እንገኝ ነበር። ለምሳሌ የዋልድባ ገዳም ሲታረስ፣ አማራዎች ከጋምቤላ እና ከጉራ ፈርዳ ሲፈናቀሉ በክስተቶቹ ላይ በርካታ ስራዎችን ሰርተናል» ይላል።
«(ሥርዓቱ) ሁሉም ዜጎች እኩል ያልነበሩበት ስለነበር እሱን ማፈራረስ ዋና ዓላማችን ነበር።» የሚለው ሙሉቀን፤ ይሄ ይሳካ ዘንድ ስለ አመፅ የሚያሳውቁ ጽሑፎችን ከማከፋፈል ጀምሮ፣ በተለያዩ የገጠር እና የከተማ አካባቢዎች ህቡዕ ቡድኖችን ማደራጀትን እንደተከተሉ ያስረዳል።
ከዚህ በተጨማሪ በየፈርጁ ነፍጥ ከጨበጡ ወገኖች ጋር የሚደረግ የመረጃ ልውውጥ፣ በማህበራዊ ገፆች የሚደረግ ቅስቀሳ የእንቅሰቃሴው አካል እንደነበር ያስገነዝባል።
«ፋኖ» እንዲደረጅ አስፈላጊውን ጫና እንዲያመጣ ያደረገው ፆታ እና ዕድሜ ባልለየ መልኩ በሁሉም የክልሉ አቅጣጫዎች የነበረው «መናበብ» እንደሆነ ሙሉቀን ያምናል። ህዝባዊ ተቃውሞው አይሎ መንግሥት የተለያዩ ለውጦችን ተግባራዊ አድርጓል። ይሄ ለውጥ ብቻውን የፋኖ ትግል ማብቂያ እንደማይሆን ሙሉቀን ያስረዳል።
«የመጣው ለውጥ መቀልበስ የማይችልበት ደረጃ ላይ እስኪደርስ ፣ተመልሰን ወደ ነበርንበት አለመግባታችንን እስክናረጋግጥ ድረስ የፋኖ ተጋድሎ ይቀጥላል !» በማለትም ያክላል።
ዘርማ "ሁሉን አሳታፊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መመስረት"
የ1997 ምርጫ ብዙ የፖለቲካ መነቃቃትን የፈጠረ ቢሆንም ምርጫውን ተከትሎ የደረሱ ማዋከቦች፣ እስሮችና የሰው ህይወት መጥፋት በጉራጌ ማህበረሰብ ውስጥ የወጣቶች እንቅስቃሴ የሆነው 'ዘርማ' ትግል መጠንሰስ ምክንያት ሆኗል።
ዘርማ በጉራጌ ማህበረሰብ ወጣት ማለት ሲሆን ከተመሰረተም አስር ዓመታት መድፈኑን ከመሪዎቹ አንዱ አሸናፊ አየለ ይናገራል። አሸናፊ እንደሚለው በአሜሪካ የተቋቋመው ዘርማ በአሁኑ ወቅት ከ30ሺ በላይ አባላት አሉት።
በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉትን ለማታገል ፌስቡክን ይጠቀማሉ። ዋናው አላማቸው መብቱን የሚጠይቅ ማህበረሰብ መፍጠር፤ በህዝቡ ላይ የሚደርሱ ግፎችን ማጋለጥና ህዝቡ መብቱንም በአደባባይ እንዲጠይቅ ማድረግ እንደቻሉ ይናገራል።
ምንም እንኳ በአገሪቱ ውስጥ እንዳሉ የወጣት እንቅስቃሴዎች መሪ የለውም ቢባልም፤ አሽናፊ እንቅስቃሴው በተደራጀ መልኩ እንደሚመራ ይናገራል። በተለያዩ የእንቅስቃሴዎች ህዝቡ አስተዳደሩ ላይ ተፅእኖ መፍጠር እንዲችል አድርገናል ብሎም ያምናል።
በአሁኑ ወቅት መንግሥት እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ የህዝቡን ድምፅ እንዲሰማና፣ ሁሉን ያካተተ ህገ-መንግሥት እንዲረቅና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መመስረትም የትግሉ ቀጣይ ሥራዎች እንደሆኑም አመልክቷል።