ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቴሬዛ ሜይ የመተማመኛ ድምጽ ሊሰጥባቸው ነው
ዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ቴሬዛ ሜይ ላይ የአስተዳደር ብቃታቸው አነስተኛ ነው በሚል ዛሬ ምሽት የመተማመኛ ድምጽ ሊሰጥባቸው ነው።
ሜይ በሚመሩት የወግ አጥባቂ (ኮንሰርቫቲቭ) ፓርቲ አባላት አማካኝነት ነው የአሰተዳደር ብቃት ጥያቄ የተነሳባቸው።
ቴሬዛ ሜይ ዛሬ ረፋድ ከቢሯቸው ፊት ለፊት በመሆን በሰጡት አጠር ባለ መግለጫ ''ድምጽ ለማግኘት ባለኝ አቅም ሁሉ እጋፈጣለሁ'' ብለዋል።
የወግ አጥባቂ ፓርቲ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ዛሬ ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ 4 ሰዓት ድረስ ድምጽ ይሰጣሉ። ውጤቱም የድምጽ አሰጣጥ ሥርዓቱ ከተጠናቀቀ ከአጭር ደቂቃዎች በኋላ ይፋ ይሆናል ተብሏል።
የቢቢሲ ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ላውራ ኩእነስበርግ እንደምትለው ከሆነ የቴሬዛ ሜይ ደጋፊ የሆኑት የሕዝብ ተወካዮች ዩናይትድ ኪንግደም ከአውሮፓ ሕብረት ለመውጣ የወሰኑት ሕዝበ ውሳኔ መዘግየት ጠቅላይ ሚንስትሯ ሥልጣን ላይ መቆየት እንዳለባቸው እንደ ምክንያት የሚያቀርበት ጉዳይ ይሆናል ትላለች።
የቴሬዛ ሜይ መንበር አደጋ ላይ ይሆን?
የመተማመኛ ድምጽ እንዲሰጥባቸው የሚጠየቁ ደብዳቤዎች ከቀረቡ በኋላ፤ ሁሉም የቴሬዛ ሜይ የካቢኔ አባላት ለጠቅላይ ሚንስትራቸው ድጋፋቸውን በጽሑፍ ገልጸዋል። ቴሬዛ ሜይን ይተካሉ ተብለው የተገመቱ ፖለቲከኞች ሁሉ ሳይቀሩ ለቴሬዛ ሜይ ድጋፋቸውን ገልጠዋል።
የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ጀረሚይ ሃንት ''ማርች 29 ላይ ከአውሮፓ ህብረት እንድንወጣ የሚያስችሉን ትክክለኛ ሰው ናቸው'' ሲሉ ቴሬዛ ሜይን የገለጿቸው ሲሆን፤ የሃገር ውስጥ ጉዳዮች ኃላፊው ሳጂድ ጃቪድ በበኩላቸው ''በአስተዳደር ብቃታቸው ላይ የተነሳው ጥያቄ ስህተት ነው ብለዋል።
በቢቢሲ ጥናት መሰረት እስካሁን ድረስ ከሕዝብ ተወካዮች መካከል 153 ያክሉ በይፋ ለቴሬዛ ሜይ ድምጻቸውን እንደሚሰጡ ያስታወቁ ሲሆን 33ቱ ደግሞ ቴሬዛ ሜይ የአስተዳደር ብቃት የላቸውም ብለው ድምጽ እንደሚሰጡ ታውቋል። ቴሬዛ ሜይ በሥልጣን ለመቆየት ቢያንስ 158 ድምጽ ማግኘት አለባቸው።
የድምጽ አሰጣጥ ሥርዓት ሚስጥራዊ ስለሆነ የድምጽ ውጤቱን ከአሁኑ መገመት አዳጋች ያደርገዋል።
ቴሬዛ ሜይ ዛሬ ምሽት ድል ከእሳቸው ጋር ከሆነ ለአንድ ዓመት ያክል የወግ አጥባቂ (ኮንሰርቫቲቨ) ፓርቲ መሪነትን ማንም አይቀናቀናቸውም።
በቂ ድምጽ የማያገኙ ከሆነ ግን ቴሬዛ የማይሳተፉበት የወግ አጥባቂ (ኮንሰርቫቲቨ) ፓርቲ መሪ ምርጫ ይካሄዳል።
ይህም ብቻ ሳይሆን ቴሬዛ ሜይ በጠባብ ድምጽ እንኳ የሚያሸንፉ ከሆነ- ከፓርቲ መሪነታቸውን በገዛ ፍቃዳቸው ይለቃሉ ተብሎ ይገመታል።
ቴሬዛ ሜይ ምን አሉ?
''ሃገራችንን ለማገልገል በአንድነት መቆም ሲገባን በመካከላችን ልዩነቶችን ስንፈጥር ሳምንታት አለፉ። ይህም በየትኛውም መንገድ ብሔራዊ ፍላጎታችንን አያስጠብቅም'' ያሉ ሲሆን ከጥቂት ዓመታት በፊት ዩናይትድ ኪንግደም (የእንግሊዝ፣ ስኮትላንድ፣ ሰሜን አየርላንድ እና ዌልስ ሃገራት ህብረት) ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት የደረሱትን ሕዝብ ውሳኔ ለማስፈጸም ከአውሮፓ ህብረት መሪዎች ጋር መልካም የሚባል ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ጨምረው ተናግረዋል።
''ጠቅላይ ሚንስትር ሆኜ ከተሾምኩበት ዕለት ጀምሮ ለብሬግዚት ጊዜ ሰጥቼ እየሠራሁ ነው፤ የጀመርኩትን ሥራም እጨርሳለሁ'' ብለዋል።
ቴሬዛ ሜይ በቂ ድምጽ ባያገኙ ዩናይትድ ኪንግድም አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር ታገኛለች?
ወዲያው አይሾምም። ወግ አጥባቂው ፓርቲ መሪውን እስኪመርጥ ድረስ ቴሬዛ ሜይ ባላደራ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ሰልጣን ላይ ይቆያሉ። ይህም እስከ ስደስት ሳምንታት ሊዘልቅ ይችላል።
ለፓርቲው መሪነት በርካታ እጩዎች የሚኖሩ ከሆነ፤ ወግ አጥባቂ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሁለት የመጨረሻ ዕጩዎች ለማስቀረት በርካታ መርጫዎችን ያካሂዳሉ።
የዩናይትድ ኪንግደም የታችኛው ምክር ቤት (ሃውስ ኦፍ ኮመንስ) ውስጥ አብላጫ ያለው ወግ አጥባቂው ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን፤ ጠቅላላ ምርጫ ሳይካሄድ የፓርቲው መሪ መንግሥት እንዲመሰርት እና ጠቅላይ ሚንስትር እንዲሆን ይጠየቃል።