አባቱ ላይ 5000 ዓመት ያስፈረደው ልጅ

በጓቲማላ እርስ በርስ ጦርነት ቤተሰቦቹ ከተገደሉበት ከ36 ዓመታት በኋላ ራሚሮ ኦሶሪዮ የተባለው ግለሰብ በጉዳዩ ዋነኛ ተጠያቂ የተባለው ሰው ላይ ፍርድ ቤት ቆሞ መስክሯል።

ነገሮችን ይበልጥ ከባድ የሚያደርገው ደግሞ የኦሶሪዮ ቤተሰቦችና የመንደሩን ሰዎች የጨፈጨፈው ሰው አሳዳጊ ኣባቱ መሆኑ ነው።

''እስካሁን ድረስ እፈራዋለሁ'' ይላል የ41 ዓመቱ ኦሶሪዮ። ''ነገር ግን እሱ ላይ መመስከር ነበረብኝ። ለቤተሰቦቼና ለመንደሬ ነዋሪዎች ሃላፊነት ይሰማኛል። ድምጻቸውን በእኔ በኩል ማሰማት አለባቸው።'' ብሏል።

እ.አ.አ. በ1982 ታህሳስ ወር ላይ 'ካይቢሊስ' በተባሉት በአሜሪካ በሰለጠኑ ታጣቂዎች የኦሶሪዮ እናትና አባት እንዲሁም ስድስት ወንድምና እህቶቹን ሲገደሉ ገና የአምስት ዓመት ህጻን ነበረ።

አሳዳጊ አባቱ ሎፔዝና ሌሎች 50 በልዩ ሁኔታ የሰለጠኑ ወታደሮች ወደ መንደሪቱ በመግባት የኦሶሪዮን ቤተሰብ ጨምሮ 200 የመንደሯን ነዋሪዎች ጨፍጭፈዋል።

በጓቲማላ ሰሜናዊ ክፍል የማያ ህዝቦች የሚኖሩ ሲሆን፤ ወታደሮቹ የተላኩት ይህንን መንደር ለማጥፋት ነበር።

ኦሶሪዮ በልጅነቱ ስላጋጠመው ነገር በደንብ ያስታውሳል። ቤተሰቦቹ ሲጮሁ፣ ጎረቤቶች የድረሱልን ጥሪ ሲያሰሙ እንዲሁም ህጻናት ሲያለቅሱ፤ ሁሉም አይረሳውም።

'' ወንዶቹን ገድለው ሲጨርሱ ወደ ሴቶች ፊታቸውን አዞሩ። በመቀጠል ህጻናቱን ገደሏቸው።'' በማለት አሰቃቂ ጊዜውን አስታውሷል።

በ1996 የእርስ በርስ ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የጓቲማላ መንግሥት በዝቅተኛ ወታደራዊ አመራር ደረጃ ላይ የሚገኙ የቀድሞ ወታደሮችን ለፍርድ ማቅረብ ጀምሮ ነበር።

የኦሶሪዮ አባት ሎፔዝ ደግሞ ከእነዚህ ወታደሮች መካከል አንዱ ነበር።

ኦሶሪዮ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንደተናገረው ወደቤታቸው ከገቡት ወታደሮች መካከል አሳዳጊው ሎፔዝ አንዱ ሲሆን፤ እናቱን እየጎተተ ከቤት አውጥቶ ከዛፍ ጋር አጋጭቶ ገድሏታል ብሏል።

ከእናቱና አባቱ በስተቀር ሌሎች የቤተሰብ አባላቱ ምን እንደሆኑ እስካሁን እንደማያውቅና ሁሌም ቢሆን እንደሚያገኛቸው ተስፋ እንደሚያደርግ ከእንባ ጋር እየታገለ ገልጿል።

ከማልቀስ ብዛት እራሱን የሳተው ኦሶሪዮ ህልም ከመሰለው ቅዠት ሲነቃ እሱና አንድ ሌላ ጨቅላ ህጻን በወታደሮቹ ተይዘው እየተወሰዱ ነበር። ለቀጣዮቹ ሳምንታትም በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ እንዲቆዩ መደረጋቸውን ያስታውሳል።

በካምፑ ውስጥ በነበረው ቆይታም አሳዳጊው ሎፔዝ ከምግቡ ቀንሶ ይሰጠውና ይንከባከበው ነበር። በመጨረሻም ከቤተሰቦቹ ጋር አብሮ እንዲኖር ሊያደርገው እንደሆነ ነገረው።

''ምንም እንኳን አዲስ ቤተሰብ በማግኘቴ ደስ ቢለኝም፤ ሎፔዝን እፈራው ስለነበረ ሁሌም ስለማምለጥ አስብ ነበር።'' ብሏል ኦሶሪዮ ለፍርድ ቤቱ።

''ለማምለጥ ብሞክር ደግሞ ካለሁበት ቦታ መጥቶ እንደሚያገኘኝና እንደሚገድለኝ ሁሌም ቢሆን ይነግረኝ ነበር።'' ብሏል።

ከብዙ ዓመታት ቆይታ በኋላም በ22 ዓመቱ የሃገሪቱን ወታደራዊ ሃይ በመቀላቀል ከአሳዳጊው የመራቅ እድል አጋጠመው። በወታደር ቤት ቆይታውም ስለ ወንድምና እህቶቹ ማጠያየቅ ጀመረ።

ጉዳዩን ሲከታተለው የነበረው የሃገሪቱ ፍርድ ቤትም ኦሶሪዮን በዋና ምስክርነት ሜኣዙን ሲያስታውቅ፤ የአሳዳጊው ቅርብ ጓደኞች የነበሩ የመከላከያ ሃይል አባላት እየፈለጉት እንደሆነ ተሰማ።

ከእነሱ ለማምለጥ ሲል ወደ ካናዳ በመሰደድ ጥገኝነት ጠየቀ። ካናዳ ውስጥ ሆኖም ጉዳዩን በቅርበት መከታተል ጀመረ።

በመጨረሳም አሳዳጊው ሎፔዝ እ.አ.አ. በ2016 በስደት ይኖርበት ከነበረው አሜሪካ ተይዞ ጓቲማላ ውስጥ ለፍርድ ቀረበ።

በወርሃ ህዳርም የሃገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የኦሶሪዮንና ሌሎች ምስክሮችን ቃል ካዳመጠ በኋላ ሎፔዝ ላይ የ5000 ዓመት እስር ፈርዶበታል።

እሱ በተሳተፈባቸው 171 የነብስ ማጥፋት ወንጀሎችም በእያንዳንዱ ሰው 30 ዓመት ነው የተበየነበት።

''ኦሶሪዯም ከአሁን በኋላ ሰላም አግኝቻለው። ቤተሰቦቼም ቢሆኑ በሰላም ያርፋሉ ብሏል።''