በትራፊክ አደጋ የበርካታ ወጣቶች ሕይወት እየተቀጠፈ ነው

የትራፊክ አደጋ በዓለም ዙሪያ ሕፃናትንና ወጣቶችን ለሞት በመዳረግ በአሁኑ ጊዜ ቀዳሚ ሆኖ እንደተመዘገበ የዓለም የጤና ድርጅት አስታወቀ።

ድርጅቱ ያወጣው አሃዝ እንደሚያመለክተው ከሆነ በአፍሪካ ከሌሎች አህጉራት በከፋ ሁኔታ በትራፊክ አደጋ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው።

የወጣው ሪፖርት እንደሚለው በርካታ የአፍሪካ ሃገራት ለተሽከርካሪዎች አስፈላጊው የፍጥነት ገደብ የላቸውም።

የመኪና አደጋዎች ዕድሜያቸው ከአምስት አስከ 29 ያሉ ሰዎችን ለሞት በመዳረግ ረገድ በዓለም ዙሪያ ቀዳሚው ምክንያት መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል።

ይህም በትራፊክ አደጋና በተያያዥ ምክንያቶች ለሞት የሚዳረጉት ሰዎች ቁጥር በኤችአይቪ/ኤድስ፣ በሳንባ በሽታ ወይም በተቅማጥ ከሚሞቱት ሰዎች የበለጠ ነው።

የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም እንዳሉት "በትራፊክ አደጋ ሳቢያ የሚመዘገቡት ሞቶች ተገቢ ያልሆነና ልናስቀረው የሚገባ ነው" ብለዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ከ100 ሺህ ሰዎች 26.6ቱ በትራፊክ አደጋ ለሞት ይዳረጋሉ። በአፍሪካ የሚያጋጥመው የመንገድ ላይ አደጋ በአውሮፓ ከሚያጋጥመው ወደ ሦስት እጥፍ በሚጠጋ መጠን ከፍ ያለ ነው ተብሏል።

አዲስ የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 1.35 ሚሊዮን ሰዎች በዓለም ዙሪያ በትራፊክ አደጋ ምክንያት ለሞት ተዳርገዋል። ይህ አሃዝም ከባለፈው ዓመት በተወሰነ መጠን ጭማሪ አሳይቷል።

በማደግ ላይ ባሉ ሃገራት ውስጥ በትራፊክ አደጋ ሳቢያ የመሞት ዕድል ከሌሎች አንፃር ሲታይ በሦስት እጥፍ ከፍ ያለ መሆኑም ተመልክቷል።

በአውሮፓ፣ በአህጉረ አሜሪካና በምዕራብ ፓሲፊክ ሃገራት ውስጥ በትራፊክ አደጋ ሳቢያ የሚመዘገበው የሞት መጠን መቀነሱ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።