ግብፃዊቷ ተዋናይት ራኒያ ዮሱፍ በአለባበሷ ምክንያት ክስ ቀረበባት

ግብፃዊቷ ተዋናይት በካይሮ በተካሄደው የፊልም ፌስቲቫል ላይ ሰውነቷን የሚያጋልጥ ልብስ በመልበሷ ክስ ቀረበባት።

ተዋናይቷ ጥቁር፣ እግሮቿን የሚያጋልጥ ቀሚስ በመልበሷ ግብፃውያንን አስቆጥቷል። በድርጊቷ ጥፋተኛ ሆና ከተገኘችም 5 ዓመት የሚደርስ እስር ሊጠብቃት እንደሚችል ተነግሯል። እርሷ ግን "አስቤበት አይደለም የለበስኩት" ስትል ይቀርታ ጠይቃለች።

የ44 ዓመቷ ተዋናይት አለባበሷ እንደዚህ መነጋገሪያ እንደሚሆን ብታውቅ ኖሮ ልብሱን እንደማትለብስ ተናግራለች።

የእርሷን ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት የወሰዱት የህግ ባለሙያዎቹ አምሮ አብደል ሳላም እና ሳሚር ሳብሪ በተመሳሳይ ድርጊት ዝነኞችን ፍርድ ቤት በማቆም ይታወቃሉ።

የተዋናይቷ አለባበስ "የማህበረሰቡን እሴት፣ ባህልና ሞራል ያላገናዘበ አንዲሁም የፌስቲቫሉን ገፅታ ያበላሸና የግብፅ ሴቶችን ያሰደበ" በማለት የህግ ባለሙያው አምሮ አብደል ተናግረዋል።

ተዋናይቷ በበኩሏ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ባስተላለፈችው መልዕክት "እንደዚህ ዓይነት ልብስ ስለብስ ይህ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነው፤ እንዲህ ዓይነት ቁጣን ይቀሰቅሳል ብዬም አልገመትኩም" በማለት አስባበት እንዳለበሰች አስታውቃለች።

እንዲህ ማለቷ ከመጠየቅ ባያስጥላትም በድርጊቷ በመፀፀት ያደገችበትን የግብፃውያን ባህልና እሴት ለመጠበቅም ቃል ገብታለች።

ሌላኛዋ የግብፅ ተዋናይ በበኩሏ እርሷ ብቻ ሳትሆን ተጋባዥ እንግዶች መድረኩን ያላገናዘበ አለባበስ ለብሰው እንደነበር ተችታለች።

ባለፈው ዓመት የግብፁ ፍርድ ቤት ድምፃዊት ሻማ አህመድ በውስጥ ሱሪ ብቻ ሆና በሙዚቃ ቪዲዮ ላይ በመታየቷና በወቅቱም ወሲብ ቀስቃሽ ሙዚቃ ባቀነቀነችበት ቪዲዮ የ2 ዓመት እስር ተፈርዶባታል፤ ምንም እንኳን በኋላ ላይ ወደ አንድ ዓመት ዝቅ ቢደረግላትም።

በተመሳሳይ መልኩ ባሳለፍነው የአውሮፓውያኖቹ ጥር ወር ላይ አምር የተባለች ድምፃዊት ያልተገባ ዳንስ በማሳየቷ በቁጥጥር ስር መዋሏ መነጋገሪያ መሆኑ የሚታወስ ነው።