ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የ'ሰከረው' ህንዳዊ ሐኪም በቀዶ ጥገና ሲያዋልድ እናትና ልጅ ህይዎታቸው እንዲያልፍ ምክንያት ሆነ
ጉጃራት በምትሰኝ የህንድ ግዛት ውስጥ ሰክሮ አንዲት እናትን በቀዶ ሕክምና ለማዋለድ የሞከረ ሐኪም በቁጥጥር ሥር መዋሉን የአካባቢው ፖሊስ ለቢቢሲ አስታወቀ።
ቀዶ ጥገናው እንደተካሄደ አዲስ የተወለደው ጨቅላ ወዲያው ሲሞት እናቲቱም ከሰዓታት በኋላ ህይወቷ አልፏል።
ፖሊስ እንደሚለው ከሆነ ሐኪሙ ላይ የተከናወነው የትንፋሸ ምረመራ ቀዶ ጥገናውን ሲያከናውን ሰክሮ እንደነበረ ተረጋግጧል።
ፖሊስ ጨምሮ እንደተናገረው የወላዷና የጨቅላው ሞት ምክንያት በሐኪሙ ቸልተኝነት ወይም በሌላ ሕክምናዊ ጉዳዮች ስለመሆኑ እያጣራሁ ነው ብሏል።
በቁጥጥር ሥር የዋለው ዶክተር ላክሃኒ፤ ልምድ ያለው ሐኪም ስለመሆኑና በዚያው ሆስፒታል ከ15 ዓመታት በላይ እንዳገለገለ ተገልጿል።
ካሚኒ ቻቺ የተባለችው እናት የምጥ ስሜት ከተሰማት በኋላ ነበር ስኞ ምሽት ወደ ሆስፒታሉ ያቀናችው።
የእናቲቱን በሰላም የመገላገል ዜና ለመስማት በጉጉት ሲጠባበቁ ለነበሩት የቤተሰብ አባላት፤ ልጁ እንደተወለደ መሞቱንና እናቲቱም ከፍተኛ የሆነ የደም መፍሰስ እንዳጋጠማት ተነግሯቸው እንደነበር የአካባቢው መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የቤተሰብ አባላቱም እናቲቱን ወደ ሌላ ሆስፒታል ይዘው ሲያመሩ ሕይወቷ መንገድ ላይ አልፏል።
አንድ የፖሊስ አባል ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሐኪሙ ለፖሊስ ደውሎ የሟች ቤተሰቦች የወላዷን ሞት ከሰሙ ሊያጠቁት እንደሚችሉ ስጋቱን በመግለጽ የፖሊስን እርዳታ ጠይቋል።
''ጥሪውን ተከታትለን በቦታው ስንደርስ ሰክሮ አገኘነው፤ ከዚያም በቁጥጥር ሥር አዋልነው'' ሲሉ የፖሊስ አባሉ አስረድተዋል።
ሆስፒታሉም የእናቲቱንና የጨቅላውን ሞት ምክንያት የሚያጣራ ኮሚቴ ማቋቋሙን አስታውቋል።