ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢንዶኔዥያ ውስጥ ዌል የተባለው የባህር እንስሳ 6 ኪሎ ያህል ፕላስቲክ ውጦ ተገኘ
ነገሩ ወዲህ ነው፤ ዌል የተባለው የባህር ላይ ግዙፍ እንሰሳ ይሞትና በማዕበል ኃይል የተገፋው በድን ሰውነቱ ኢንዶኔዥያ በሚገኝ አንድ ባህር ዳርቻ ላይ ይገኛል።
አጋጣሚ ሆኖ የባህር ዳርቻው የአንድ ብሔራዊ ፓርክ አካል ነበርና የፖርኩ ሰዎች የዌሉን ሆድ በቀደዱ ጊዜ መዓት ኩባያ ያያሉ።
6 ኪሎ ያህል ይሆናል የተባለ የፕላስቲክ ዓይነት የተገኘበት ይህ ዌል 'ታይዋን ተራ' የሚል ቅፅል ስያሜ እየተሰጠው ነው።
115 ኩባያ፤ አራት የፕላስቲክ ጠርሙስ፤ 25 የፕላስቲክ ፌስታል እና ሁለት ነጠላ ጫማዎች።
9.5 ሜትር ርዝመት ያለው ይህ እንሰሳ ሆዱ ውስጥ መዓት ፕላስቲክ መገኘቱ የአካባቢ ጥበቃ ሰዎችን እያስቆጣ ነው።
ኢንዶኔዥያዊቷ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ ድዊ ሱፕራፕቲ ሁኔታውን «እጅግ ደስ የማያሰኝ» ሲሉ ይገልፁታል።
ባለሙያዋ እንሰሳው ሊሞት የቻለው በፕላስቲኮች ምክንያት ነው ባንል የፕላስቲኮች አለመፈጨት ከጊዜ በኋላ ሕይወቱን ሊያሳጡት እንደሚችሉ እሙን ነው የሚል አመክንዮ ያስቀምጣሉ።
ኢንዶኔዥያን ጨምሮ በሌሎች የእስያ ሃገራት መልሰው ጥቅም ላይ የማይውሉ ፕላስተኮች ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።
የዓለማችን የውሃ አካላት ከጊዜ ጊዜ በፕላስቲክ ዕቃዎች እየተበከሉ ነው፤ ቻይና፣ ኢንዶኔዥያ፣ ፊሊፒንስ፣ ቪየትናም እና ታይላንድ ለዚህ ጥፋት 60 በመቶ ያህል ድርሻ ያዋጣሉ።
ፕላስቲክ የባህር ላይ ፍጡራንን ሕይወት ከሚቀጥፉ ነገሮች እንደአንሱ መሆን ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል።