ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"በኢትዮጵያ 93 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ መጸዳጃ ቤት የለውም"
ዛሬ ታስቦ በዋለው የዓለም የመጸዳጃ ቤት ቀን በወጣ አንድ ዘገባ በኢትዮጵያ 93 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ መሠረታዊ መጸዳጃ ቤት በቤቱ እንደማያገኝ ተገለጸ።
ዘገባውን ያወጣው "ዎተር ኤይድ" የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው።
ለዜጎቿ መሠረታዊ የመጸዳጃ ቦታ ባለማቅረብ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች ቀዳሚ ሆናለች። ባለፈው ዓመትም በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ከዓለም እጅግ የከፋ የመጸዳጃ ቤት አቅርቦት ችግር ያለባት አገር ሆና ተመዝግባ ነበር።
ቻድ፣ ማዳጋስካርና ደቡብ ሱዳን 90 ከመቶ የሚሆነው ሕዝባቸው በቂ መጸዳጃ ቦታን አያገኝም። ጎረቤት ኤርትራ 83 በመቶ ሕዝቧ በመኖሪያ ቤት ውስጥ መጸዳጃ ቤት እንደማያገኝ ዎተር ኤይድ ያጠናቀረው ጥናታዊ ዘገባ ያስረዳል።
ከሰሀራ በታች ብቻ 340 ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝብ በቂና መሠረታዊ የመጸዳጃ አገልግሎትን አያገኝም። ይህም ለተቅማጥና ሌሎች ውሀ ወለድ በሽታዎች ያጋልጠዋል።
የዓለም የመጸዳጃ ቀን ታስቦ በዋለበት በዛሬው ዕለት በወጣው በዚህ ዘገባ መሠረት በአህጉሪቱ ትምህርት ቤቶች በቂ መጸዳጃ ቤቶች ባለመኖራቸው 60 ከመቶ የሚሆኑ ሕጻናት ለችግር ይዳረጋሉ።