የደህንነት ተቋሙ ምክትል የነበሩት አቶ ያሬድ ዘሪሁን ፍርድ ቤት ቀረቡ

የቀድሞው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ኃላፊ እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል አቶ ያሬድ ዘሪሁን ፍርድ ቤት ቀረቡ።

አቶ ያሬድ ዘሪሁን ትናንት ሌሊት 5 ሰዓት ላይ በዱከም ከተማ ኮኬት ተብሎ በሚጠራው ሆቴል ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተዘግቦ ነበር።

ተጠርጣሪው አቶ ያሬድ በዛሬ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት ቀርበዋል።

ሰሞኑን በሙስናና በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ ከ60 የሚበልጡ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ደህንነትና መረጃ አገልግሎት ምክትል ሃላፊ የነበሩት አቶ ያሬድ ዘሪሁን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅላይ አቃቤ ህግ ብርሃኑ ፀጋዬ በትዊተር ገፃቸው ላይ አረጋግጠዋል።

ኢቢሲ እንደዘገበው አቶ ያሬድ ዘሪሁን በቁጥጥር ስር የዋሉት ትናንት ህዳር 5 ከምሽቱ 5 ሰዓት ላይ ወደ ኬንያ ለመሸሽ ሲሞክሩ በፌደራል ፖሊስና በኦሮሚያ ፖሊስ ክትትል ዱከም ከተማ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በወቅቱም 22ሺህ ብር ፣ ሁለት መታወቂያ እና መንጃ ፈቃድ ይዘው መገኘታቸውን ዘገባው ጨምሮ ገልጿል።

አቶ ያሬድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው ተሾመው የነበረ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ማለትም ከአንድ ወር በኋላ በጤና እክል ምክንያት በአቶ ዘይኑ ጀማል መተካታቸው የሚታወስ ነው።

አቶ ያሬድ ወደ ፌደራል ፖሊስ ከመሄዳቸው በፊት ለረጅም ጊዜ በደህንነት ተቋሙ በምክትል ሃላፊነት ያገለገሉ ሲሆን የቀድሞ የተቋሙ ዋና ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋም ቀኝ እጅ እንደነበሩ ይነገራል።

ተጠርጣሪውን አቶ ያሬድ ለማስመለጥ ሞክረዋል የተባሉት የነፍስ አባታቸውና ሾፌራቸው ትናንት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት ቀርበው ነበር።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ማክሰኞ ሕዳር 3 ቀን 2011 ዓ. ከስልሳ በላይ በሚሆኑ ተጠርጣሪዎች ላይ ከሰብዓዊ መብት ጥሰትና ከሙስና ጋር በተያያዘ የተሰሩ ወንጀሎችን በተመለከተ ያደረገውን ምርመራ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።