ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፈረንሳያዊ እናት ልጇን ለሁለት አመት ያህል ኮፈን ውስጥ በመደበቋ ተከሰሰች
ፈረንሳያዊቷ እናት ልጇን በመኪናዋ ኮፈን ውስጥ በመደበቅ ተከሰሰች።
ህፃኗ የተገኘችው መኪናዋ ጋራዥ ልትጠገን በመጣችበት ወቅት አንድ መካኒክ ድምፅ በመስማቱ ነው።
እናቷም በህፃኗ ላይ ጥቃትን በማድረሷና ለእድሜ ዘላቂ የሆነ የአካል ጉዳት በማድረስ እስከ 20 አመት እስራት ይጠብቃታል።
እርግዝናዋንና እንዲሁም መውለዷን ከህይወት አጋሯና ከሶስት ልጆቿ እንደደበቀችም ተገልጿል።
ሮዛ ማሪያ ዳ ክሩዝ የተባለችው ይህቺ ግለሰብ ቱሌ በምትባለው ከተማ ክስ የቀረበባት ሲሆን፤ ልጇን በአንድ ክፍል በመደበቅና በኮፈን ውስጥ ታቆያት ነበር ተብሏል።
በአውሮፓውያኑ 2013 የተገኘችው ይህች ህፃን ልጅ የሁለት ዓመት ዕድሜ ያላት ሲሆን በምግብ እጥረትና በመቀንጨር ላይ እንደነበረች ሪፖርቶች ያሳያሉ።
ህፃኗን ያገኛት መካኒክ በበኩሉ የመኪናውን ኮፈን ሲከፍት መጥፎ ጠረን እንዳወደውና፣ ግርጥት ያለች፣ የተራቆተችና በሰገራ የተጨማለቀች ህፃን ልጅ እንዳገኘ ተናግሯል።
የ50 ዓመት ዕድሜ ያላት ፖርቹጋላዊቷ እናት ፖሊስ በጠየቃት ወቅት "ልጅ እንዳልሆነችና ቁስ እንደሆነች ገልፃለች።
የሰባት ዓመት እድሜ ያላት ይህች ህፃን በአሁኑ ወቅት በማደጎ ውስጥ ነው ያለችው።
ሁለት ወንድሞቿና እህቷ ለጥቂት ጊዜ በማደጎ ውስጥ ቆይተው ወደ ቤተሰቦቻቸው ቤት ተመልሰዋል።
የህይወት አጋሯ በበኩሉ ስለ ህፃኗም ሆነ ስለ እርግዝናው ምንም ባለማወቁ በነፃ ተሰናብቷል።
የፍርድ ሂደቲ ከ5 እስከ 7 ቀናት ይወስዳል ተብሏል።