ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጉርሻ፡ በዓለም ዙሪያ ምን ይመስላል?
ሰሞኑን የእንግሊዝ ፖለቲከኞች ስለ ብሬግዚት (ኢንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት የመለየት ጉዳይ) ከመነጋገር ውጪ ሌላ ጉዳይ ላይኖራቸው ይችላል ብለን ልናስብ እንችላል።
• አንድ በሞቴ!
ሆኖም ግን በዚህ ሳምንት ፖለቲከኞች ካፌዎች እና ምግብ ቤቶች ለሠራተኞቻቸው ጉርሻ እንዳይሰጡ ስለመከልከል ሲወያዩ ቆይተዋል።
በዚህ ጉዳይ እንደ እንግሊዞች ነገሩን በጥሞና የተነጋገረበት ሃገር ግን የለም። በ17ኛው ክፍለ ዘመን እንግሊዞች ጉርሻ መስጠት እንደጀመሩ ይታመናል። ተግባሩም የተጀመረው ለዝቅተኛው የማህበረሰብ ክፍል ስጦታ የመለገሻ ተግባር ተደርጎ ነበር።
አሁን ጉርሻ መስጠት በዓለም ዙሪያ ልማድ ሆኗል። ይሁን እንጂ በአንዳንድ ሃገራት ጉርሻ መስጠት እንደ ስድብ ሊቆጠር ይችላል።
አሜሪካ
ጉርሻ ከመስጠት ቀጥሎ ግብር ሰነድ ቅጽ መሙላት ነው የሚያደናብረው እየተባለ መቀለድ በአሜሪካ የተለመደ ሆኗል።
አሜሪካውያን ወደ አውሮፓ መጓዛቸውን ተከትሎ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ጉርሻ መስጠት በአሜሪካ ተለመደ። ይህ ልማድ ፀረ-ዲሞክራሲ ነው፤ ሠራተኞችንም እንደ ለማኝ ይቆጥራል ተብሎ ብዙም ድጋፍ አልነበረውም።
21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ግን በአሜሪካ ጉርሻ የደመወዝ ዋና አካል ተደርጎ ይቆጠራል። ኦፈር አዛር የተባሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ እ.አ.አ በ2007 ከምግብ ቤቶች ብቻ ሠራተኞች በጉርሻ መልክ 42 ቢሊየን ዶላር እንደተቀበሉ ይናገራሉ።
ቻይና
ልክ እንደ ብዙ እስያዊ ሃገራት ቻይና ውስጥ ጉርሻ የመስጠት ባህል እምብዛም ነው። እንዲያውም ለአስተናጋጆች የሚሰጠው ጉርሻ እንደ ጉቦ ተቆጥሮ ለዘመናት ተግባሩ የተከለከለ ነበር። ዛሬም ቢሆን ተግባሩ ብዙም አልተለመደም።
የሃገሪቱ ነዋሪዎች በሚያዘወትሯቸው ምግብ ቤቶች ጉርሻ አይሰጥም። በውጪ ሃገር ዜጎች በሚጎበኙ ሆቴሎች ውስጥ ግን ልማዱ እየተስፋፋ ነው።
ጃፓን
ለሠርግ፣ ቀብር እና ለተለያዩ ሁነቶች ጉርሻ መስጠት የተለመደ ቢሆንም በሌላ ሃገራት በተለመደው መልኩ ገንዘብ መስጠት ግን ተቀባዩን የማሳነስ ስሜት ይፈጥራል።
ፍልስፍናው ተጠቃሚው ጥሩ አገልግሎት እና መስተንግዶ ማግኘት የተለመደ መሆን አለበት የሚል ነው። ጉርሻ መስጠት ግድ ከሆነ ጉርሻው ሲሰጥ በፖስታ ተደርጎ አክብሮትን በሚያሳይ መልኩ መሆን አለበት።
በጃፓን የሚገኙ የሆቴል ውስጥ አስተናጋጆች ፍጹም ጨዋ፣ ሰዓት አክባሪ እና ጉርሻ አክብሮት በተሞላበት መልኩ አልቀበልም ኢንዲሉ ስልጠና ይሰጣቸዋል።
ፈረንሳይ
አስተናጋጆች የተሻለ ደመወዝ እንዲያገኙ እና ጉርሻ ከመቀበል እንዲቆጠቡ በማሰብ ፈረንሳይ ምግብ ቤቶች በሂሳብ ላይ የአገልግሎት ክፍያን (ሰርቪስ ቻርጅ) እንዲጨምሩ የሚያስገድድ ሕግ አወጣች። ይህም በጊዜ ሂደት ውስጥ በሌሎች የአውሮፓ ሃገራት እየተለመደ መጣ።
ወጣቶች ብዙውን ጊዜ ጉርሻ እንደማይሰጡ ቢነገርም ጉርሻ መስጠት ግን አልቀረም። እ.አ.አ በ2014 15% የሚሆኑት የፈረንሳይ ተጠቃሚዎች ጉርሻ እንደማይሰጡ ተናግረዋል። ይህም ቁጥር ከዓመት በፊት ከነበረው ቁጥር በሁለት እጥፍ ጨምሯል።
ደቡብ አፍሪካ
እ.አ.አ 2017 በደቡብ አፍሪካ በየቀኑ 140 መኪናዎች ተሰርቀዋል። የሥራ ፈላጊው ሕዝብ ቁጥር 25 በመቶ በሆነባት ደቡብ አፍሪካ፤ በሌሎች ሃገራት ባልተለመደ መልኩ ለመኪና ጥበቃ ጉርሻ ይሰጣል።
ሹፌሮች የማቆሚያ ቦታ እንዲያገኙ ከመርዳት አንስቶ መኪናቸውን እስከመጠበቅን ያካትታል።
ስዊዘርላንድ
በስዊዘርላንድ ያሉ ተጠቃሚዎች ለምሳሌ ገንዘብ ጠቅልለው ለሆቴል ሠራተኞች ወይም ለፀጉር አስተካካዮች ይሰጣሉ ይባላል። ሆኖም ግን የሃገሪቱ ዝቅተኛው ክፍያ ከዓለም ዙሪያ ከፍተኛው ነው። ለምሳሌ የአስተናጋጅ ደመወዝ በወር ከ4000 ዶላር ይበልጣል።
ሕንድ
የሕንድ ምግብ ቤቶች እና ካፍቴሪያዎች በሚያስከፍሉት ዋጋ ላይ ተጨማሪ የአገልግሎት ክፍያ ስለሚጠይቁ ጉርሻ መስጠት ተጨማሪ ወጪ ነው።
ከዚህ ውጪ በሕንድ ያለው ልማድ የሂሳቡን 15% ወይም 20% መተው ነው። እ.አ.አ በ2015 በተደረገ ጥናት መሰረት ከእስያ ሃገራት ሕንዶች ከባንግላዴሺ እና ከታይላንዶች ቀጥሎ ከፍተኛ ጉርሻ በመስጠት የታወቁ ናቸው።
ሲንጋፖር
ለሆቴል ሰራተኛ ውይም ለታክሲ ሹፌር አንስተኛ ጉርሻ መስጠት አያስቆጣም። ይሁን እንጂ ጉርሻ መስጠት በራሱ በሲንጋፖር ብዙ የሚያነጋግር ጉዳይ ነው። በሃገሪቱ የመንግሥት ድረ-ገጽ ላይ 'ጉርሻ መስጠት የደሴቱ የኑሮ ዘይቤ አይደለም' የሚል ጽሑፍ አለ።
ግብፅ
ጉርሻ መስጠት በግብፅ ባህል ውስጥ በጣም የሰረፀ ሲሆን፤ ጉርሻ ባክሺሽ በመባል ይታወቃል። አቅም ያላቸው ግብፃውያን እንደ አስተናጋጅና ቤንዚን ቀጂ ላሉ ሠራተኞች በየጊዜው ጉርሻ ይሰጣሉ።
ይህም ባህል የሥራ እጦት ቁጥር 10% በሆነበት ኢኮኖሚ ውስጥ በጣም ተመስጋኝ ነው። ጉርሻም የሃገሪቱን ጠቅላላ የሃገር ውስጥ ምርት 40% ያክላል።
ኢራን
ኢራንን ለመጎብኘት የሚሄዱ ሰዎች ታሩፍ የተሰኘውን ባህል ያገኛሉ። እሱም በኢራን ባህል ማንኛውንም ክፍያ በጨዋነት በመጀመሪያ እምቢ ማለት ሲሆን፤ የታክሲ ሹፌርም ጭምር በመጀመሪያ የሚሰጠውን ክፍያ አይቀበልም።
ይህ ግን ለጉርሻ አይደረግም ምክንያቱም ጉርሻ የዕለት ተዕለት ኑሮ አካል ሆኗል።
ሩስያ
በሶቪየት ዘመን ጉርሻ መስጠት ጭራሽ አይቻልም ነበር። ምክንያቱም የሠራተኛውን ክፍል እንደማሳነስ ተደርጎ ስለሚቆጠር ነው።
ሩስያውያን ግን ስም አላቸው እሱም 'ሻዬቪዬ' ሲሆን 'ለሻይ' እንደ ማለት ነው።
ጉርሻ መስጠት እ.አ.አ በ2000ዎቹ ተመልሶ ቢመጣም በእድሜ የገፉ ሰዎች ግን አሁንም እንደ ስድብ ሊቆጥሩት ይችላሉ።
አርጀንቲና
ቆንጆ ምግብ ላቀረበ አስተናጋጅ ጉርሻ ቢሰጡ ችግር ውስጥ ባይከትዎትም እንኳን እ.አ.አ በ2004 በወጣው የሰራተኛ ሕግ መሠረት ግን ለምግብ አቅራቢና ለሆቴል ኢንዱስትሪ ጉርሻ መስጠት ሕጋዊ አይደልም ይላል።
እንደዚያም ሆኖ ግን ጉርሻ አሁንም ይሰጣል ይህም የአንድን አርጀንቲናዊ አስተናጋጅ ውርሃዊ ገቢ 40% ያህላል።