ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኩዌት ባለስልጣን በፓኪስታን ዲፕሎማት የኪስ ቦርሳቸው ተሰረቀ
በፓኪስታን ከፍተኛ የመንግስት ተቀጣሪ የሆነ ሰው የኩዌት ልኡካን ቡድን አባል ያስቀመጠውን የኪስ ቦርሳ ሲሰርቅ የሚያሳይ ምስል ከተለቀቀ በኋላ ፓኪስታን በሰውዬው ላይ ምርመራ መጀመሯን አስታውቃለች።
ነገሩ ይባስ ብሎ በሃገር ውስጥ መገናኝ ብዙሃን እና በማህበራዊ ሚዲያዎች ተጠርጣሪው ዛራር ሃይደር ክሃን ይሄ ነው ተብሎ የተለቀቀው ምስል ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው በአሜሪካ የሚኖር ሰው ነው።
የፓኪስታን የመረጃ ሚኒስትሩ ፋዋድ ቻድሪይ እንዳሉት ተጠርጣሪው በሃገሪቱ የኢንዱስትሪና ምርት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ ከፍተኛ ሃላፊነት ያለው ተቀጣሪ ሲሆን፤ ሃገሪቱን የማይወክል ተግባር እንደሆነ ገልጸዋል።
የፓኪስታን መንግስት እንዳስታወቀው አቶ ሃይደር ከስራቸው ተሰናብተዋል፤ ተግባሩም መላው የሃገሪቱን ዜጎችና መንግስትን ያዋረደ ነው ብሏል።
በኩዌትና ፓኪስታን መካከል የንግድ ሁኔታዎችን ለመነጋገር ፓኪስታን የገባው ልኡካን ቡድን አባል የሆኑት ሰው የኪስ ቦርሳቸውን የተቀመጡበት ጠረጴዛ ላይ ትተውት የሄዱ ሲሆን፤ ተጠርጣሪውም የኪስ ቦርሳቸውን ሲያነሳ በተንቀሳቃሽ ምስል ተቀርጿል።
የኪስ ቦርሳቸው መጥፋቱን ያስተዋሉት የኩዌት ሃላፊም ጉዳዩን ለፓኪስታን ሃላፊዎች አሳውቀው፤ ተጠርጣሪው መታወቁን በሰሙ ጊዜም አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድና ማንነቱ እንዲነገራቸው ጠይቀዋል።
በቦርሳው ውስጥም ጠቀም ያለ የኩዌት ዲናር እንደነበረ አንድ የፓኪስታን ጋዜጣ ዘግቧል።
እጅግ በፈጠነ ሁኔታ ታዋቂነትን ያተረፈው የኪስ ቦርሳው ሲሰረቅ የሚሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል በሃገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችም ጭምር የታየ ሲሆን፤ ብዙ ፓኪስታናውያን አዋረደን በማለት ቁጣቸውን እየገለጹ ነው።
መልኩን በደንብ መለየት በማይቻለው ተንቀሳቃሽ ምስል ምክንያት ተጠርጣሪ ተብሎ ፎቶው በመገናኛ ብዙሃን የቀረበው ሰው ግን ዛራር ሃይደር ሳይሆን አሜሪካ ውስጥ የአደጋ መከላከል ባለሙያ የሆነውና ተቀራራቢ ስም ያለው ዛይድ ሃይደር ነው።
በተለይ ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያዎች በተሰራጨው የተሳሳተ የዛይድ ሃይደር ምስል ስር ብዙ ፓኪስታናውያን ቁጣቸውን በስድብና አዋረድከን መልዕክቶች እየገለጹ ነው።
በጉዳዩ ዙሪያ የተጠየቀው የአሜሪካ ነዋሪው '' እኔ ምንም የማውቀው ነገር ነገር የለም፤ ስሜ ዛራር ሃይደር ሳይሆን ዛይድ ሃይደር ነው።'' ብሏል። እስካሁንም ግን የተጠርጣሪው ዛራር ሃይደር ትክክለኛ ምስል አልተገኘም።
በፓኪስታን የተንሰራፋውን የሙስና ችግር ለማጥፋት እዋጋዋለሁ ብለው ከሁለት ወራት በፊት የተመረጡት የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ክሃን ገና ከጅምሩ ያልጠበቁት አጋጣሚ ወዳጃቸው ኩዌትን አስቆጥቶባቸዋል።