ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የደሞዙን 100 እጥፍ በስህተት የተከፈለው ሰው ''ይቅርብኝ'' አለ
በአውስትራሊያ የሚገኙ አንድ የመንግስት ተቀጣሪ ሰው የገንዘብ ክፍል ሰራተኞች በሰሩት ስህተት የደሞዛቸውን 100 እጥፍ በአንድ ጊዜ አግኝተዋል።
ስህተቱ የተፈጠረው በቁጥሮቹ መካከል ነጥብ በሚገባበት ጊዜ እንደሆነም ታውቋል።
ሰራተኛው ሊከፈለው ይገባ የነበረው 4921 ዶላር ከ76 ሳንቲም ሲሆን፤ በቁጥሮቹ መካከል ያለቦታዋ የገባችው ነጥብ ግን ደሞዙን ወደ 492 ሺህ 176 ዶላር ከፍ እንዲል አድርጋለች።
ስህተቱ እንደተፈጠረ የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ጉዳዩን ለአካባቢው የኦዲተር ቢሮ አሳውቀዋል።
በስራ ምክንያት ወደ ሰሜናዊ የሃገሪቱ ክፍል ራቅ ብሎ ተጉዞ የነበረው ሰው ያላሰበውና ያልገመተው ዓይነት ገንዘብ ወደ ባንክ ደብተሩ ሲገባ ትንሽ ቢደናገጥም፤ ምንም ሳያንገራግር ለመንግስት ለመመለስ ወስኗል።
ይህኛው አጋጣሚ የመጀመሪያው እንዳልሆነና፤ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ተመሳሳይ 743 ስህተቶት እንደተሰሩ የኦዲተር ቢሮ ሃላፊው ገልጸዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም በተመሳሳይ ክስተቶች እስካሁን 767 ሺ ዶላር ሳይመለስ እንደቀረ ጨምረዋል።