በቡሩንዲ ርዕሰ-መምህሩ ለተማሪ ሲፈተኑ በፖሊስ ተያዙ

በቡሩንዲ የሚገኝ የአንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ-መምህር ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ተማሪዎች መውሰድ ያለባቸው ፈተና ላይ በአንድ ተማሪ ስም ወደ ፈተና ክፍል ገብተው ሲፈተኑ ተይዘዋል።

በዋና ከተማዋ ቡጁምቡራ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኘው ቡቴሬሬ የቴክኒክ ኮሌጅ ርዕሰ-መምህር የሆኑት ቤንጃሚን ማኒራምቦና የመጨረሻውን የፈተና ወረቀት እየሰሩ ሳለ ነበር ፖሊስና የሃገሪቱን የትምህርት ሚኒስትርን ጨምሮ ባለስልጣናት ወደፈተናው አዳራሽ በመግባት ያፋጠዋቸዋል።

እጅ ከፍንጅ ተይዘው ማምለጫ ያላገኙት ርዕሰ-መምህሩ ቤንጃሚን ማኒራምቦና የፈፀሙትን ወንጀል እዚያው ፈተና አዳራሽ ውስጥ አምነው ተናዘዋል።

ድርጊቱን ለምንና ለማን እንደፈፀሙ ሲጠየቁም፤ ሠላም ለማስከበር ወደ ሶማሊያ ለተሰማራ የቡሩንዲ ወታደር እየተፈተኑ እንደነበርና እሱም ከግዳጅ ሲመለስ ለውለታቸው ገንዘብ እንደሚሰጣቸው ቃል እንደገባላቸው ተናግረዋል።

"የምትለው በሙሉ ውሸት ነው፤ ወደ እስር ቤት ትወሰዳለህ" ሲሉ ከፖሊሶች ጋር በስፍራው የነበሩት የቡሩንዲ ትምህርት ሚኒስትር ጃንቪየር ንዲራሂሻ ተናግረዉታል።

ፖሊስ ስለድርጊቱ ጥቆማ ካገኘ በኋላ ርዕሰ-መምህሩን ሲያጭበረብሩ ከተገኙ ሌሎች ተማሪዎች ጋር እንደያዛቸው ተገልጿል።

ጨምረውም "ምርመራ እናካሂዳለን ምክንያቱም ይህንን ስታደርግ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳልሆነ ሰምተናል" ሲሉ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ከፖሊስ በተጨማሪ ሚኒስትሯን ተከትለው ዜናውን ለመዘገብ በርካታ ሪፖርተሮች በፈተናው ስፍራ ተገኝተው ነበር።

ርዕሰ-መምህሩ ፈተና በማጭበርበር ከተጠረጠሩ አራት ተማሪዎች ጋር የተያዙ ሲሆን፤ አንደኛው ተማሪ ርዕሰ-መምህሩን ከተባለው ወታደር ጋር አገናኝቷል በሚል ተከሷል።

ርዕሰ-መምህሩ ቤንጃሚን ማኒራምቦና በፖሊስ ቁጥጥር ስር ይገኛሉ።

ቡሩንዲ ውስጥ ወሳኝ ብሔራዊ ፈተናዎችን የሚወስዱ ተማሪዎች ከትምህርት ቤታቸው ውጪ በሌላ ትምህርት ቤት ውስጥ ስለሆነ ቤንጃሚን ማኒራምቦናም ፈተና በወሰዱበት ስፍራ ሊታወቁ አልቻሉም ነበር።