ታይዋናዊ ቱሪስት ኬንያ ውስጥ ፎቶ ሊያነሳው በነበረው ጉማሬ ተነክሶ ሞተ

ታይዋናዊ ቱሪስት ኬንያ ውስጥ ጉማሬ ፎቶ ለማንሳት ሲሞክር ጉማሬው ደረቱ ላይ ነክሶ ገድሎታል። የ 66 ዓመቱ ቻንግ ሚንግ ቻውንግ 'ሌክ ናይቫሻ' በተሰኘው የዱር እንስሳት ማቆያና መዝናኛ ውስጥ ነበር ጉማሬውን ፎቶ ለማንሳት የሞከረው።

ጉማሬው ሌላ ታይዋናዊም ነክሷል። የአይን እማኞች እንደተናገሩት ሁለቱ ቱሪስቶች ጉማሬውን ፎቶ ለማንሳት በጣም ተጠግተውት ነበር። ህይወቱ ያለፈው ጎብኚ በጉማሬው ከተነከሰ በኃላ ወደ ህክምና መስጫ ቢወሰድም ብዙ ደም ስለፈሰሰው ሊተርፍ አልቻለም።

ው ፔንግ ቴ የተባለው ሌላው ታይላንዳዊ የደረሰበት ጉዳት ለክፉ የሚሰጥ አልነበረም። የኬንያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ቱሪስቶቹ ቻይናውያን ናቸው ብለው ቢገምቱም የኃላ ኃላ የታይዋይን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ታይዋናውያን መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የሌክ ናይቫሻ ባለ መርከቦች ማህበር አስተዳዳሪ ዴቪድ ኪሎ ለኬንያው ስታር ጋዜጣ እንደተናገሩት የአካባቢው ሐይቅ የውሀ መጠኑ ከፍ ስላለ ጉማሬዎች ከሐይቅ እንዲወጡ ግድ ብሏቸዋል። ከሐይቁ ወጥተው በሆቴል አቅራቢያ ስለሚዘዋወሩም በቀላሉ ከሰዎች ጋር ይገናኛሉ።

ከአጥቢ እንስሳት መካከል እጅግ አደገኛው ጉማሬ ነው። በአካባቢው በዚህ ዓመት ብቻ ስድስት ሰዎች በጉማሬ ተገድለዋል።

ጉማሬዎች እስከ 2,750 ኪሎ ግራም ድረስ ሊመዝኑ ይችላሉ። አፍሪካ ውስጥ በየዓመቱ 500 ሰዎች በጉማሬ ተበልተው ይሞታሉ።

ታይዋናዊው ጎብኚ የሞተባት ኬንያ አምና 1.4 ሚሊዮን ሰዎች ጎብኝተዋት ከቱሪዝም 1.2 ቢልየን ዶላር ገቢ አግኝታለች።