ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አስራ አምስት ዓመታት በዋሻ ውስጥ የታገተችው ኢንዶኔዥያዊት ታዳጊ ነፃ ወጣች
የኢንዶኔዥያዋ ሱላወሲ ከተማ ፖሊስ እንደገለጸው ለ15 ዓመታት በዋሻ ውስጥ ታግታ የቆየች የ28 ዓመት ሴት ነጻ አውጥቷል።
አንድ የ83 ዓመት ሰው አፈናውን እንደፈጸመ የተጠረጠረ ሲሆን፤ ሴትየዋ ገና የ13 ዓመት ታዳጊ እያለች ነበር በግዳጅ ወደ ዋሻው ያመጣት። ሴትየዋ እንደገለጸችው በልጅነት እድሜዋ በመንፈስ የተሞላ እንደሆነ አሳምኗት ቆይቶ ነበር።
ለብዙ ዓመታትም በምሽት ወደ ቤቱ እየወሰደ ጾታዊ ጥቃት ይፈጽምባት እንደነበርም ተናግራለች።
በአካባቢው የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ሰውዬው ሃይማኖታዊ ፈውስ የሚሰጥና የባህላዊ ህክምና ባለሙያ መሆኑን እየዘገቡ ነው።
እ.አ.አ በ2003 ጥቃቱ የተፈጸመባት ሴት የ13 ዓመት ታዳጊ እያለች ለህክምና ተብሎ ወደ ተጠርጣሪው ቤት በቤተሰቦቿ መወሰዷንና በዛው መቅረቷን ፖሊስ ገልጿል።
ሰውዬው በጾታዊ ጥቃትና የህጻናት መብት ጥሰት ክስ ቀርቦበታል።
ለህክምና ወደ ሰውዬው ቤት በሄደችበት ያልተመለሰችውን ልጃቸው የት እንደሄደች ሲጠይቁት የተሻለ ስራ ፍለጋ ወደ ሃገሪቱ መዲና ጃካርታ መሄዷን እንደገለጸላቸው ታውቋል።
ቤተሰቦቿና ሌሎች ዘመዶች ታዳጊዋን ለመፈለግ ጥረት ቢያደርጉም ሊሳካላቸው ስላልቻለ ለፖሊስ ጠፍታብናለች ብለው አስታውቀው ነበር።
ፖሊስ እንደገለጸው ከሆነ ባለፈው እሁድ ሴትየዋን በአንዲት ትንሽ ዋሻ ውስጥ ተገኝታለች። በዋሻው ውስጥም አንዳንድ የቤት ውስጥ መገልገያዎችን ማግኘቱንም ጨምሮ ገልጿል።
ታዳጊዋ ለማምለጥ ብትሞክር እሱ የሚቆጣጠረው መንፈስ ጉዳት እንደሚያደርስባትና ቤተሰቦቿንም እንደሚከታተላቸው ስለነገራት በፍርሃት ለማምለጥም ሆነ ቤተሰቦቿን ለማግኘት አለመሞከሯን ተናግራለች።
ተጠርጣሪው ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ 15 ዓመት ድረስ የእስር ቅጣት ሊጠብቀው እንደሚችል ተገልጿል።