የአሜሪካው ኤፍ ቢ አይ በቦምብ ፍንዳታው ምርምራ ላይ መሰማራቱ ተገለፀ

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን በሀገሪቱ ላይ እያከናወኗቸው ላሉ በጎ አስተዋፅኦዎች ለመደገፍ በወጡበት ሰልፍ በደረሰ የቦምብ ጥቃት ሁለት ሰዎች ሲሞቱ፣ ከመቶ በላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የጥቃት አድራሾቹን ማንነት ለማወቅ ምርመራ እንደተጀመረ ፖሊስ ገልፆ የአሜሪካው ኤፍቢአይም በምርመራው ስራ ላይ እንደተሰማራ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ዘይኑ ጀማል ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በሀገር ውስጥም አደጋውን ለማጣራት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች የተውጣጣ አንድ ቡድን የተቋቋመ መሆኑንም ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል ጨምረው ተናግረዋል።

"ምርመራው በጅምር ላይ ሲሆን እስካሁን ያለው ሂደት ጥሩ ነው" ብለዋል።

የዚህን ቡድን ስራ ለመደገፍ ደግሞ የተሻለ ልምድ እና የተሻለ ቴክኖሎጂ ያላቸው የሌሎች ሃገራት የፖሊስ ተቋማት ቡድኑን በማገዝ ስራ ላይ ለማሳተፍ እቅድ መያዙንም ተናግረዋል።

ለጊዜው በፈቃዳቸው የመጡት የአሜሪካው ኤፍ ቢ አይ መሆናቸውንምና ከቡድኑ ጋር በስራ ላይ መሰማራታቸውንም ገልፀዋል።

እስካሁን ባለው ሂደትም 28 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጨምረው ተናግረዋል።