ጎርፍ ሲከሰት መደረግ ያለባቸው አምስት ጥንቃቄዎች

ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ በጣለው በረዶ የቀላቀለ ከፍተኛ ዝናብ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።

በመዲናዋ በተለያዩ ስፍራዎች በተከሰቱ የጎርፍ አደጋዎች መኖሪያ ቤቶች እና ተሸከርካሪዎች በጎርፍ ተውጠው ታይተዋል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአስኮ፣ አደይ አበባ፣ ጀርመን አደባባይና ጎልፍ ክለብ ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች በደረሰው የጎርፍ አደጋ ጉዳት ማጋጠሙን ገልጸው አሁንም የአየር ትንበያ መረጃዎች በመጪዎቹ ቀናት ከፍተኛ መጠን ያለዉ የዝናብ ስርጭት ስለሚኖር ነዋሪው አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ መልክት አስተላልፈዋል።

ለመሆኑ ጎርፍ ከመከሰቱ እና ከተከሰተ በኋላ መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች ምንድናቸው?

ነዋሪዎች ጎርፍ ከመከሰቱ በፊት እና ከተከሰተ በኋላ የሚከተሉትን 5 ዝግጅቶችን ቢያደርጉ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት መቆጣጠር ወይም መቀነስ ይቻላል።

1. ማዳሪያዎችና ሌሎች ከረጢቶችን በአሸዋ ሞልቶ ከበር ደጃፍ ላይ መደርደር

እንደ አማራጭ ጎርፍ ወደ ቤት እንዳይገባ፤ በቤት ዙሪያ የውሃ መፍሰሻ ቦይ ወይንም ጉድጓድ መቆፈር ይችላሉ። በርና መስኮቶችን በደንብ መዝጋቶን አይዘንጉ።

2. እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ያለበትን ሁኔታ ያጣሩ

እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ያለበትን ሁኔታ ማወቅ ሌሎች ጥንቃቄዎችን በተረጋጋ መንፈስ ለማድረግ ይጠቅማል። የታሰሩ የቤት እንስሳት ካሉ መፍታት እንዳይረሱ።

3. በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ማንኛውም መጠቀሚያዎችን ከሶኬት ላይ ይንቀሉ

ከጎርፍ አደጋ ጋር ተያይዞ ስዎች ሊጠነቀቁት የሚገባ ነገር የኤሌክትሪክ አደጋ ነው። ከቤት ውስጥ ባለፈ በውጪም ቢሆን የወደቁ የኤሌክትሪክ ሽቦዎች ካሉ ጥንቃቄ ያድርጉ።

የተቆፈሩ ጉድጓዶች ካሉ ሰዎች ገብተው እንዳይወድቁ በደንብ ይክደኗቸው።

4.ቆሻሻ ወደ ውጪ እንዳይወጣ መጸዳጃ ቤቶችን በደንብ ይዝጉ

እንደ ጸረ ተባይ እና የመሬት ማዳበሪያ ያሉ መርዝነት ያላቸው ነገሮችን ጎርፉ የማይደርስበት ከፍ ወዳለ ቦታ ያስቀምጧቸው። ምክንያቱም የተበከለ ውሃ ሌላ ተጨማሪ በሽታ ይዞ ሊመጣ ይችላል።

5. ከፍ ወዳለ ቦታ ይሂዱ፤ አልያም የቤትዎ ጣራ ላይ ይውጡ

የጎርፍ አደጋ በሚያጋጥሞት ጊዜ ቤት ውስጥ ሆነው ራሶን መከላከል ካልቻሉ፤ ወደ ጣራ ላይ ወይንም ከፍ ወዳለ ቦታ ይውጡ። ጎርፍ ውስጥ መራመድ አይመከርም።