በተሰማሩበት ሙያ ስኬትዎን የሚወስኑ 6 የሰብዕና መገለጫዎች

ጉጉ፣ ጠንቃቃ እና ተፎካካሪ ነዎት? ከሁኔታዎች ጋር ቶሎ የመላመድ፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መቋቋም እና ግራ መጋባትን አምኖ መቀበልን የመሰሉ ምስጢራዊ ችሎታ አለዎት?

እንግዲያውስ እንኳን ደስ አለዎ! በሥነ-ልቦ ባለሙያዎች በተደረገ ጥናት መሰረት እነዚህ ስድስቱ መገለጫዎች በህይወትዎ እና በሚሰሩት ሥራ ስኬታማ እንዲሆኑ ያደርጋሉ።

እውነታው ግን አንዳንድ ልዩነቶች አሉት። እነዚህ ባህሪያት ሲበዙ ደግሞ ውጤታማነትዎን ሊቀንሱ ይችላሉ። ስለዚህ የስኬት ሚስጥሩ በሁለቱ ፅንፎች መካከል ሚዛንን ጠብቆ መቆየት መቻል እና ጠንካራ እና ደካማ ጎንን ለይቶ ማወቅ ነው።

ይህ አቀራረብ በሥራ ባህሪያችን ላይ ጫና የሚያሳድሩ የተወሳሰቡ የሥነ-ልቦና መገለጫዎችን ለመረዳት ይረዳል። ከዚህ በፊት የሥራ አካባቢ ባህሪያትን ለማወቅ የተደረገው ጥረት አከራካሪ ውጤቶች አስገኝቷል።

በሥነ-ልቦናው ዘርፍ የተገኙ ስኬቶች በሥራ አካባቢ ውጤታማ ያደርጋሉ የሚለውን ግኝት ከግምት ውስጥ በማስገባት የለንደን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎቹ ኢየን መክሪ እና ኤድሪየን ፈርሃም በተሰማሩበት ሙያ ስኬታማ የሚያደርጉ ስድስት የስብዕና መገለጫዎችን አስቀምጠዋል።

መክሪ እንደሚለው እያንዳንዱ መገለጫዎች የራሳቸው የሆነ ውስንነት እና ጠንካራ ጎን አላቸው።

ስለዚህ የእያንዳንዱ መገለጫ ጥቅም የሚወሰነው ግለሰቦች በሚሰሩት ሥራ ላይ ስለሆነ መለኪያው ከእያንዳንዱ ሁኔታ ጋር ይቀያየራል።

ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት እነዚህ ስድስት የስብዕና መገለጫዎች እንዴት ወደ ስኬት እንደሚወስዱ እንመልከት

1. ጠንቃቃነት

ጠንቃቃ ሰዎች ሁሌም እቅዳቸውን በትክክል ይተገብራሉ።

የእያንዳንዱ ውሳኔያቸው የወደፊት ውጤት ተጽዕኖን ያውቃሉ። ስሜታቸውንም መቆጣጠር ይችላሉ። ከአእምሮ ብቃት ምዘና ፈተና በኋላ ይህ የጠንቃቃነት ባህሪ በህይወትዎ ስኬታማ ለመሆን ወሳኝ ነው።

በሥራ አካባቢ ለትንሽ ነገሮች ትኩረት መስጠት ስልታዊ በሆነ መልኩ እያንዳንዱን ሥራ ለማቀድ ይጠቅማል።

2. ከነገሮች ቶሎ መላመድ

ሁሉም ሰው የሚያስጨንቀው ነገር ያጋጥመዋል፤ ዋናው ጥያቄ ግን እንዴት ያልፈዋል የሚለው ነው። ይህ ማለት ሥራዎት እና ሌላ ህይወትዎ ላይ ጫና እንዳሳያሳድር ለመላመድ መሞከር ማለት ነው።

ይህ ባህሪ የሌላቸው ሰዎች የሥራ አካባቢ አፈጻጸማቸው ደካማ ነው። ነገር ግን ተገቢውን የሥነ-ልቦና እርምጃ ከወሰዱ ውጤታማ መሆን ችላሉ።

ብዙ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ውጤታማ ለመሆን ሲባል አስጨናቂ ጉዳዮች ላይ በደንብ ትኩረትን መስጠት ከተቻለ፤ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ያለ ሰው ያሰበውን ነገር ማሳካት ይችላል።

3. ግራ መጋባትን አምኖ መቀበል

የጥያቄዎን መልስ የሚያውቁበት አይነት ሥራ ነው የሚወዱት ወይስ ግራ የሚያጋባ እና አስጨናቂ የሥራ ቦታ?

የማያውቁትን ነገር የማይፈሩ እና ግራ መጋባትን አምነው የሚቀበሉ ሰዎች የተሻለ ውሳኔ ለመወሰን ይችላሉ። ብዙ ነገሮችንም ከግምት ውስጥ ያስገባሉ።

ይህ ባህሪ ትንሽ አምባገነናዊ ወደ ሆነ አስተሳሰብ ይመራል ይላል መክሪ። እንደዚህ አይነት ሰዎች ትንሽ የምትባለው ነገር ትርጉም እስከምትሰጣቸው ድረስ ስለሚጨነቁ የራሳቸውን ውሳኔ የመጨረሻ አድርገው ሊወስዱ ይችላሉ።

ግራ መጋባትን አምኖ መቀበል የሚችል ሰው ለማንኛውም አይነት ለውጥ ሁሌም ዝግጁ ነው። ግራ መጋባትን አምኖ አለመቀበል ግን ሁሌም መጥፎ ነው ማለት አይደለም።

4. ጉጉ መሆን

ከሌሎች ባህሪያት ጋር ሲነጻጸር በሥነ-ልቦና አጥኚዎች ዘንድ ጉጉት ብዙ ትኩረት አልተሰጠውም።

ነገር ግን በቅርብ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የማናውቀውን ነገር ለማወቅ ያለን ጉጉት ሁሌም አዲስ ነገር ለመፍጠር ይረዳናል። ይህ ማለት ለአዳዲስ ነገሮች ክፍት የሆነ ጭንቅላት አለን ማለት ሲሆን፤ በምንሰራው ሥራ ደስተኞች እንድንሆን ይረዳናል።

አንዳንዴ ግን የበዛ ጉጉት ወዳልተፈለገ የጊዜ ብክነት ሊወስደን ይችላል።

5. አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መቋቋም

ደስ የማይል ነገር ሲያጋጥምዎት ለጊዜው ስለቀለልዎት ብቻ ዝም ብለው ያልፋሉ ወይስ ምቾት ባይሰጦትም ጉዳዩን ተጋፍጠው ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ይሞክራሉ?

ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች ጋር እራስን ማላመድ መቻል ወደፊት ወደ አመራር ቦታ እንድንመጣ እና ለብዙ ነገሮች ውሳኔ መስጠት እንድንችል ይረዳናል።

6. ተፎካካሪ መሆን

ለስኬት ሲባል የሚደረግ ትንቅንቅ እና ጤናማ ያልሆነ ፉክክር ወይም ቅናት ትልቅ ልዩነት አላቸው።

ፉክክር ሁሌም ለበለጠ ሥራ የሚያነሳሳ ሲሆን፤ ተጨማሪ ጥረት እንድናሳይና እቅዳችንን እንድናሳካ ሊረዳን ይችላል። ሲበዛ ግን የቡድን ሥራዎችን ያስተጓጉላል።

እነዚህ ስድስቱ ባህሪያት በአንድነት በሥራ ገበታችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አላቸው። በተለይ ደግሞ ወደ አመራር ቦታ መምጣት ለሚፈልጉ ሰዎች።

ምንም እንኳን ጥናቱ ገና ባያልቅም ከላይ የተዘረዘሩት የሰዎች ባህሪያት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የሥራችንን ፍሬ እና ውጤታማነታችንን ለመለካት ይረዱናል።

በመጨረሻም ተፎካካሪነት እና ግራ መጋባትን አምኖ መቀበል ከሁሉም በተሻለ ተቀባይነትን ያገኙ ሲሆን፤ የተሻለ ገቢ እንደሚያስገኙም ተጠቁሟል።