ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአንድ ቤተሰብ አባላት የተቀነባበረው የሽብር ጥቃት
ከአንድ ቀን በፊት ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶችን ያስተናገደችው የኢንዶኔዢያዋ ሱባራያ ከተማ ዛሬ ደግሞ በሞተር ሳይክል ላይ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች በፖሊስ ዋና መስሪያ ቤት ላይ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ፈጽመውባታል።
በፍንዳታው የፖሊስ ሃይል አባላት ጉዳት ያስተናገዱ ሲሆን ለጥቃቱ አይኤስ ሃላፊነቱን እወስዳለሁ ብሏል።
የኢንዶኔዢያው ፕሬዝደንት ጆኮ ዊዶዶ ጥቃቶቹን ''የፈሪ ተግባር፣ ክብር የሌለው እና ኢ-ሰብዓዊ'' ሲሉ ገልጸዋል።
የዛሬው ጥቃት እሁድ ከተፈጸመው ጥቃት ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ የተነገረ ነገር የለም።
በእሁዱ ጥቃት ምን ተፈጸመ?
የትናንቱ ሶስቱ ፍንዳታዎች በአንድ ቤተሰብ አባላት የተቀነባበሩና በከተማዋ የሚገኙ ቤተክርስቲያናቶችን ኢላማ ያደረጉ ነበሩ።
ፖሊስ እንዳለው የቤተሰብ አባላቱ አይኤስ ከሶሪያ መንግሥት ጋር ወደሚፋለምበት የሶሪያ የጦር ቀጠና አምርተው ወደ ኢንዶኒዢያ ተመልሰዋል።
የቤተሰብ አባላቱ ወደ ሶሪያ ተጉዘዋል ይባል እንጂ የጦር ተሳትፏቸው ምን ያህል እንደሆነ የተነገረ ነገር የለም።
ወላጅ አባት ዲታ ኦፕሪአረቶ ተብሎ የሚጠራ ግለሰብ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን በኢንዶኔዢያ የአይኤስ ተልዕኮን ለማሳካት የተቋቋመ ኔትዎርክ መሪ ነበር።
የቤተሰብ አባላቱ በፈጸሙት የመጀመሪያ ጥቃት የ16 እና 18 ዓመት እድሜ ያላቸው ወንድማማቾች ከጠዋቱ 1፡30 ላይ ሞተር ሳይክል እያሽከረከሩ ወደ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በመግባት ተሸክመው የነበረውን ተቀጣጣይ ፈንጂ አፈነዱ።
ከዚያም ወላጅ አባት ባለቤቱን እና ሁለት ሴት ልጆቹን ቤተክርስቲያን አቅራቢያ አወረዳቸው። የ9 እና 12 ዓመት ዕድሜ ያለቸው ሴት ልጆች ከእናታቸው ጋር በመሆን ታጥቀው የነበሩትን ፈንጂ እላያቸው ላይ አፈነዱ።
በሶስተኛው ጥቃት ደግሞ፤ ወላጅ አባት መኪናው በማሽከርከር ወደ መሃል ከተማ ካቀና በኋላ፤ ፈንጅ የተጠመደበትን መኪናው ውስጥ እንዳለ በሌላ ፔንቴኮስታል ቤተክርስቲያን ላይ ፍንዳታ ፈጸመ።
በጥቃቶቹ 13 ሰዎች ሲገደሉ ከ40 ባለይ ሰዎች ደግሞ ጉዳት አስተናግደዋል። ይህ ጥቃት በኢንዶኔዢያ ከ10 ዓመት በኋላ የደረሰ አስከፊ የሽብር ጥቃት ሆኖ ተመዝግቧል።
እሁድ ረፋድ ላይ ደግሞ በመኖሪያ ህንጻ ላይ በደረሰ ጥቃት ሶስት ሰዎች መገደላቸውን ኤኤፍፒ የዜና ምንጭ ዘግቧል።