በሎስ አንጀለስ እየተዛመተ ያለው ሰደድ እሳት ወደ ዝነኛው የሆሊውድ ምልክት እየተቃረበ ነው

በሎስ አንጀለስ በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ ያለው ሰደድ እሳት ወደታዋቂው የሆሊውድ ምልክት እየተቃረበ ነው።

የሰደድ እሳቱ የሆሊውድ ምልክት በሚገኝበት የሆሊውድ ኮረብታማ ስፍራዎች ላይ እየተያያዘ መሆኑን ከስፍራው የወጡ ቪዲዮዎች አሳይተዋል።

እሳቱ እየተያያዘ ካለበት ስፍራ ነዋሪዎች ለቀው እንዲወጡ ረቡዕ ምሽት የተላለፈውን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ በሆሊውድ ጎዳና ላይ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ እና ትርምስ ታይቷል።

በሎስ አንጀለስ ረጅም ርቀትን የሚሸፍነው 'ሰንሴት ቦሎቫርድ' የተሰኘው ታዋቂ አውራ ጎዳና የሚገኙ ህንጻዎች በእሳት ቃጠሎው መጎዳታቸውን የሎስአንጀለስ ታይምስ ዘገባዎች አመልክተዋል

ነዋሪዎች በጎዳናው ለአስርት ዓመታት ያዘወትሯቸው የነበሩ ባንኮች፣ ካፌዎች እና ትልልቅ የገበያ መደብሮች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ገልጸዋል።

አንድ የእሳት አደጋ ኃላፊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በሆሊውድ ኮረብታማ ስፍራዎች ላይ የተነሳው እሳት በፍጥነት እየተዛመተ እንደሆነ እና ይህንን የመቆጣጠር እድሉ ዜሮ እንደሆነም ነው ያስረዱት።

ፓሪስ ሂልተን በሰደድ እሳቱ ቤታቸውን ካጡ ታዋቂ ሰዎች መካከል አንዷ ናት።

በሎስ አንጀለስ ታሪክ አውዳሚ በሆነው በዚህ የሰደድ እሳት አምስት ሰዎች መሞታቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከ137 ሺህ ሰዎች በላይ ተፈናቅለዋል።

እሳቱ በሎስ አንጀለስ ከተማ የትኛውም ስፍራ እየተዛመተ ያለ የሚመስል ሲሆን ከተማዋ የዓለም በእሳት እየጋየች ያለች እንደምትመስል የቢቢሲ ዘጋቢ ይናገራል።

በሎስ አንጀለስ እና በአጎራባች ግዛቶች ቢያንስ አምስት ሰደድ እሳቶች የተያያዙ ሲሆን ሶስቱን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አልተቻለም።

ፓሊሳድስ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሰደድ እሳት በሎስ አንጀለስ የተቀሰቀሰው ማክሰኞ እለት ሲሆን በግዛቲቷ ትልቁ ነው። የፓስፊክ ፓሊሳድስ አካባቢን ጨምሮ ከ17 ሺህ 200 ሄክታር በላይ የሚሸፍን ሰፊ ግዛት አውድሟል። ኢቶን የተሰኘው ደግሞ በሰሜናዊ የሎስ አንጀለስ እን አልታዴና ባሉ ከተሞች እየተዛመተ የሚገኝ ሲሆን 10 ሺህ 600 ሄክታርን መሬት በመሸፈን በግዛቲቷ ሁለተኛው ትልቁ እሳት ሆኗል።

ሶስተኛው ሰደድ እሳት ኸረስት የሚሰኝ ሲሆን ማክሰኞ እለት ተከስቶ ከሳን ፈርናንዶ በስተሰሜን በኩል እየተዛመተ ይገኛል። ይህም እሳት 855 ሄክታርን ይሸፍናል። ሌላኛው ሊዲያ ረቡዕ ከሰዓት በኋላ በሎስ አንጀለስ በስተሰሜን ተራራማዋ አክቶን አካባቢ ተቀስቅሶ ወደ 350 ሄክታርን መሬት በመሸፈን ተዛምቷል።

ባለስልጣናቱ 40 በመቶው የሰደድ እሳት በቁጥጥር ስር መዋሉን ባለስልጣናት ተናግረዋል። ረቡዕ ምሽት በሆሊውድ ኮረብታማ ስፍራዎች የተከሰተው ሰንሴት የሚሰኝ ሲሆን ከሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ወደ 20 ሄክታር እያደገ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት ወደ 43 ሄክታር ተዛምቷል። ሌሎቹ ውድሌይ እና ኦሊቫስ የተሰኙት ሰደድ እሳቶች በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአካባቢው የእሳት አደጋ ባስልጣናት ገልጸዋል።