ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአማጺው ቫግነር ቡድን መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ሩሲያ ውስጥ እንደሚገኝ ተነገረ
ከሳምንት በፊት ለአጭር ጊዜ የቆየውን የትጥቅ አመጽ ሩሲያ ውስጥ ያካሄደው የቫግነር ቅጥረኛ ቡድን አዛዥ የቭጌኔ ፕሪጎዢን የሚገኘው እዚያው ሩሲያ ውስጥ መሆኑን ቤላሩስ አስታወቀች።
አመጹን ተከትሎ በደቡባዊ ሩሲያ ውስጥ ታይቶ የነበረው የቅጥረኛው ቡድን መሪ ፕሪጎዢን፣ አስካሁን ያለበትን ቦታ በተመለከተ በእርግጠኝነት የታወቀ ነገር አልነበረም።
አመጽ እና ፍጥጫውን ባስቆመው በቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ አማካይነት በተደረሰው ስምምነት መሠረት ፕሪጎዢን ላይ የቀረበው የአገር ክህደት ክስ ተነስቶ ወደ ቤላሩስ እንዲሄድ እንደተፈቀደለት ተነግሮ ነበር።
ከሳምንት በፊት የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት የቭጌኒ ፕሪጎዢን ከሩሲያ ወጥቶ ወደ አገራቸው መግባቱን ተናግረው ነበር።
ስምምነቱ ከተደረገ ከቀናት በኋላም የቫግነር ቡድን መሪ የግል ጄት አውሮፕላን ወደ ቤላሩስ ዋና ከተማ ሚኒስክ ስትበር የታየች ቢሆንም፣ ፕሪጎዢንን በውስጧ ስለማሳፈሯ ግን ታወቀ ነገር አልነበረም።
ነገር ግን የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት ሉካሼንኮ ዛሬ ሐሙስ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “ፕሪጎዢንን በተመለከተ፣ በአሁኑ ወቅት የሚገኘው ሴንት ፒተርስበርግ [ሩሲያ] ውስጥ ነው። በቤላሩስ ግዛት ውስጥ የለም” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም የተወሰኑ የቫግነር ቅጥረኛ ቡድን ተዋጊዎች ቤላሩስ ውስጥ እንዲሰፍሩ ያቀረቡት ሐሳብ እንዳለ ሲሆን፣ ይህም የቤላሩስ አጎራባች በሆኑ የኔቶ አባል አገራት ላይ ስጋት ፈጥሯል።
የቫግነር ቡድን የግል ቅጥረኛ ወታደሮች ያሉት ሠራዊት ሲሆን፣ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር እያካሄደችው ባለው ጦርነት ውስጥ ከአገሪቱ መደበኛ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ ሲዋጋ ቆይቷል።
ፕሪጎዢን የቡድኑን ተዋጊዎች በመጠቀም በሩሲያ ላይ አመጽ ባካሄደበት ወቅት፣ ዩክሬን ውስጥ የነበሩ ተዋጊዎቹን በማንቀሳቀስ በደቡባዊ ሩሲያ በምትገኘው ሮስቶቭ-ኦን-ዶን በተባለችው ከተማ ያሉ አንዳንድ የደኅንነት ማዘዣ ማዕከላትን ተቆጣጥሮ ነበር።
ከዚያም በኋላ አማጺያኑ ወደ ዋና ከተማዋ ሞስኮ ማምራት በመጀመራቸው፣ የሩሲያ መንግሥት ሞስኮን ጨምሮ በበርካታ የአገሪቱ ግዛቶች ውስጥ የደኅንነት ጥበቃውን አጠናክሮ ነበር።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም በወቅቱ ቡድኑን በአገር ክህደት የከሰሱት ቢሆንም፣ አመጹን ለማስቆም በተደረሰው ስምምነት ለቡድኑ መሪ ፕሪጎዢን የደኅንነት ዋስትና በመስጠት በቫግነር ቡድን ላይ የቀረነበው የወንጀል ክስ ውድቅ ተደርጓል።
የቡድኑ ተዋጊዎችም የሩሲያ ጦርን ለመቀላቀል ኮትራት እንዲፈርሙ፣ ካልፈለጉ ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ወይም ወደ ቤላሩስ እንዲሄዱ አማራጭ ቀርቦላቸዋል።