ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አርቴታ ሁለት ፍጹም ቅጣት ምት ተከልክለናል ሲሉ በብስጭት ተናገሩ
የአርሰናል አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ቡድኑ ትናንት ከኒውካስል በነበረው ጨዋታ ሁለት ፍጹም ቅጣት ምት ተከልክለናል አሉ።
የአርሰናል ተጫዋቾች ባሳዩት አቋም “በጣም ኮርቻለሁ” ያሉት አርቴታ ‘በሚያበሳጭ’ ሁኔታ ሁለት ፍጹም ቅጣት ምት ተከልክለናል ብለዋል።
ትናንት ምሽት አርሰናል እና ኒውካስል ዩናይትድ በኢሚሬትስ ስታዲየም ያደረጉት ውጥረት የሰፈነበት ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።
ጥቁር እና ነጭ ለባሾቹ ኒውካስሎች 90 ደቂቃ ሙሉ ጠንክረው በመከላከል የጎል በራቸውን ሳያስደፍሩ ወጥተዋል።
በትናንት ምሽቱ ጨዋታው አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ በዳኛ ውሳኔ እየተበሳጩ ከመሃል ዳኛ እና ከአራተኛው ዳኛ ጋር ሲነታረኩ በተደጋጋሚ ታይተዋል።
ከአሰልጣኙ በተጨማሪ የአርሰናል ተጫዋቾች ከመሃል ዳኛው ውሳኔ ጋር ባለመስማማት ቅሬታቸውን ሲገልጹ አምሽተዋል።
አርሰናል ቅጣት ምት አግኝቶ ተከላካዩ ገብርኤል ማጋሌስ በኒውካስሉ ተከላካይ ዳን በርን ተጎትቶ የተጣለበት እንዲሁም ተቀይሮ ወደሜዳ የገባው ጃኮብ መርፊ ኳስ በእጁ የነካ የሚመስልበት አጋጣሚ ለቡድናቸው ፍጹም ቅጣት ምት ማሰጠት የነበረባቸው አጋጣሚዎች ናቸው ብለዋል አሰልጣኙ።
“ሁለት ፍጹም ቅጣት ምቶች ነበሩ። . . . እያወራሁ ያለሁት ስላየሁት ነገር ነው። ሁለት የሚያበሳጩ ፍጹም ቅጣት ምቶች” ብለዋል አርቴታ።
በቢቢሲ ሬዲዮ 5 ጨዋታውን በቀጥታ ሲያስተላልፍ የነበረው ማቲው አፕሰን ሁለተኛው የፍጹም ቅጣት ምት ጥያቄ የተነሳበት መርፊ፤ ኳሷን በእጁ የነካው እጁ በተፈጥሯዊ ቦታ ከሰውነቱ ሳይርቅ እየወደቀ እያለ ስለሆነ ፍጹም ቅጣት ምት ሊሆን አይችልም ብሏል።
የኒውካስል አሰልጣኝ ኤዲ ሃው እና የቀድሞ የማንችስተር ዩናይትድ ተከላካይ ጋሪ ኔቪል በተመሳሳይ ይህ ፍጹም ቅጣት ምት ሊሆን አይችልም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ይሁን እንጂ ጋሪ ኔቪል በመጀመሪያው ክስተት አርሰናል ፍጹም ቅጣት ምት አለማግኘታቸው “ሊያበሳጫቸው” ይችላል፤ ኒውካስልም እድለኛ ነበር ብሏል።
የመሃል ዳኛው አንዲ ማድሊ በትናንት ምሽት ጨዋታ 9 ቢጫ ካርዶችን የመዘዙ ሲሆን በዳኝነታቸው ደስተኛ ያልነበሩት የአርሰናል ደጋፊዎች ቅሬታቸውን ሲያሰሙባቸው ነበር።
‘አርሰናል ሊጉን ሊያሸንፍ ይችላል’
መድፈኞቹ ከኒውካስል አቻ ቢለያዩም አሁንም ሊጉን በ8 ነጥብ ልዩነት እየመሩ ይገኛሉ። ባለፉት 11 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችም አልተሸነፉም።
“አርሰናሎች ሊጉን ሊያሸንፉ ይችላሉ፤ ነገር ግን ይህ እንዲሆን የዝውውር ገበያው ውስጥ መግባት አለባቸው። . . . ይህን ሊግ ማሸነፍ የሚችሉት በዝውውር ገበያው አጥቂ ማግኘት ከቻሉ ነው” ብሏል ጋሪ ኔቪል።
አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ቡድናቸው “እንደዚህ መጫወት ከቀጠለ፣ የዚህ አይነት አቋም የሚያሳይ ከሆነ ብዙ ጨዋታዎችን እናሸንፋለን” ብለዋል።
በዝውውር መስኮቱ ክለቡን ለማጠናከር ትኩረት እንደሚያደርግም አሰልጣኙ ተናግረዋል።
መድፈኞቹ የሻካታር ዶኔስክ የክንፍ ተጫዋች ሚካይሎ ሙድሪክ ለማስፈረም ስለመቃረባቸው ዘገባዎች እያመላከቱ ነው።
‘በጣም ጥሩ የመከላከል ጨዋታ’
የኒውካስል አሰልጣኝ ኤዲ ሃው በኢሚሬትስ ከነበራቸው ጨዋታ በኋላ በሰጡት አስተያየት “በጣም ጥሩ የመከላከል ጨዋታ አሳይተናል” ብለዋል።
አሰልጣኙ ተጫዋቾቻቸው ጥሩ የቡድን ጨዋታ እና የጋራ ጥረት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ኒውካስል ባለፉት 13 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች አልተሸነፈም። በተከታታይ ስድስት ጨዋታዎች ደግሞ ግብ አልተቆጠረባቸውም።
አርሰናል 17 ጨዋታ አድርጎ በ44 ነጥብ ሊጉን እየመራ ሲሆን ሲቲ 16 ተጫውቶ በ36 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ኒውካስል ደግሞ 18 ጨዋታ አድርጎ 35 ነጥብ በመያዝ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።