በቀይ ባህር ላይ መርከቦችን እያጠቁ ያሉት የየመን ሁቲ አማጽያን እነማን ናቸው?

ከጋዛው ጦርነት ጋር ተያይዞ በስፋት ስማቸው እየተነሳው ያሉት የሁቲ አማጽያን ናቸው።

ሰፊውን የየመንን ክፍል የቆጣጠሩት የሁቲ አማጽያን ቀይ ባህርን አቋርጠው ወደ እስራኤል የሚጓዙ መርከቦችን የጥቃት ኢላማ እንደሚያደርጉ አስጠንቅቀዋል።

በህዳር ወር ላይም ባለቤትነቱ የእስራኤላዊ ነው የተባለ የጭነት መርከብ በቀይ ባህር አግተዋል።

ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ሌሎች የንግድ መርከቦችም ላይ ሮኬቶች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ጥቃት ፈጽመዋል።

የሁቲ አማጽያን እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ እርዳታ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲገባ እንዲሁም እስራኤል በጋዛ ላይ እየፈጸመችው ያለውንም የማያባራ ጥቃት እንድታቆም ጠይቀዋል።

የሁቲዎች ጥቃት በእስራኤል ኢላማዎች ላይ

እስራኤል በሐማስ ለተፈጸመብኝ ጥቃት አጸፋዊ ምላሽ ነው በሚል የማያባራ ጥቃት መጀመሯን ተከትሎ የሁቲ አማጽያን በርካታ ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል አስወንጭፈዋል።

እንዲሁም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖችንም) እንዲሁ ተኩሰዋል።

አሜሪካ በቀይ ባህር ላይ ያሉትን የጦር መርከቦች በመጠቀም የተወሰኑትን በማክሸፍ ሌሎቹን ደግሞ በቀይ ባህር ላይ እና በግብጽ ላይ እንዲያርፉ በማድረግ አቅጣቸውን አስቀልብሻለሁ ብላለች።

ህዳር ወር ላይም ባለቤትነቱ የእስራኤል ነው ያሉትን የጭነት መርከብ በቀይ ባህር ላይ በማገት በየመን ባህር ዳርቻ ወደሚገኝ ቦታ ወስደውታል።

እስራኤል በበኩሏ መርከቧ የእሷ እንዳልሆነች አስታውቃ ከመርከቡ ሰራተኞችም መካከል አንድም እስራኤላዊ ዜግነት የለውም ብትልም ያልተረጋጋጡ ዘገባዎችን ባለቤቱ እስራኤላዊ ሳይሆን አይቀርም ብለዋል።

ከህዳር መጨረሻም ጀምሮ ሁቲዎች በቀይ ባህር ባህር ላይ በሚጓዙ በርካታ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።

አማጽያኑ ተቆጣጥረዋቸው በሚገኙት ከየመን ዳርቻ በተወነጨፉ ባለስቲክ ሚሳኤሎች እንዲሁም ድሮኖች ነው ጥቃቶቹን የፈጸሙት።

በቀይ ባህር ላይ የሚገኙት የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ እና የፈረንሳይ የጦር መርከቦች አብዛኞዎቹን ማክሸፍ እንዲሁም አቅጣጫ ማስቀየስ ቢችሉም ብዙ መርከቦችም በጥቃቱ ተመትተዋል።

ይህንንም ተከትሎ የዓለማችን ግዙፍ የመርከብ ጭነት መጓጓዣ አገልግሎት ሰጪ ሜዲትራኒያን ሺፒንግ ካምፓኒ የመርከቦቹን አቅጣጫ እንደቀየረ እና ይህንንም መንገድ መጠቀም እንደሚያቆም አስታውቋል።

ይህ ኩባንያ ብቻ አይደለም የፈረንሳዩ ኩባንያ ሲኤምኤ ሲጂኤም፣ እንዲሁም ሌላኛው ግዙፍ የመርከብ ጭነት አጓጓዥ የሆነው የዴንማርኩ መርስክ፣ የጀርመኑ ሃፓግ ሎይድ እና ነዳጅ አምራቹ ቢፒ (ብሪቲሽ ፔትሮሊየም) ለደህንነታቸው በመስጋት በቀይ ባህር በኩል አናልፍም ብለዋል።

በመከከለኛው ምስራቅ የአሜሪካ ወታደራዊ ዘመቻን የሚያካሂደው ሴንትኮም የተባለው ኩባንያ “እነዚህ ጥቃቶች የሚሰነዘሩት በየመን ሁቲዎች ቢሆንም ሙሉ በሙሉ የሚደገፉት በኢራን ነው” ብሏል።

አሜሪካ የንግድ መርከቦችን ከተጨማሪ የሁቲ ጥቃቶችን ለመከላከልም የባህር ኃይል ግብረ ኃይልም ለማቋቋም ሃሳብ አቅርቧል።

የሁቲ አማፂያን እነማን ናቸው? አላማቸውስ ምንድን ነው?

ሁቲዎች የየመን ታጣቂ ቡድን ሲሆኑ መሰረታቸውም ዛይዲስ በመባል የሚታወቁት የሃገሪቱ የሺዓ ሙስሊም ነው።

ቡድኑ በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ሲቋቋምም የወቅቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት አሊ አብደላህ ሳሌህ አገዛዝ የተንሰራፋውን ሙስና ለመዋጋት በሚል ነበር።

ስማቸውንም የወሰዱት ከንቅናቄው መስራች ከሆኑት ሁሴን አል ሁቲ ነው። ራሳቸውንም ‘አንሳር አላህ’ ወይም የአምላክ ደጋፊዎች ብለው ይጠራሉ።

በአሜሪካ መሪነት ምዕራባውያኑ ኢራቅን መውረራቸውንም ተከትሎ ሁቲዎች “አምላክ ታላቅ ነው፣ ሞት ለአሜሪካ፣ ሞት ለእስራኤል። እርግማን ለአይሁዶች፣ ድል ለእስልምና’ የሚልም መፈክርን ማሰማት ጀመሩ።

እስራኤል፣ አሜሪካ እና ሰፊውን ምዕራባዊ ክፍል የሚቃወም እና በኢራን የሚመራው ‘አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ ጥምረት’ መሆናቸውንም አስታወቁ። ከሁቲ በተጨማሪ ሐማስ እና ሂዝቦላህ የዚህ ጥምረት አካል ናቸው።

ሁቲዎች በአሁኑ ወቅት በባህረ ሰላጤው ወደ እስራኤል የሚያቀኑትን መርከቦች ላይ ጥቃት እየፈጸሙ ያሉበትንም ምክንያት እንደሚያብራራም በአውሮፓ የሰላም ኢንስቲትዩት የየመን ተንታኝ ሂሻም አል ኦምሴ ያስረዳሉ።

“በአሁኑ ወቅት ከኢምፔሪያሊስቶች ጋር እየተዋጉ ነው፤ የእስላም አገራት ጠላቶች ጋር እየተዋጉ ነው” የሚሉት ምሁሩ “ይህም ከመሰረታቸው ጋር የሚጣጣም” እንደሆነም ያስረዳሉ።

ሁቲዎች ሰፊውን የየመንን ክፍል እንዴት ተቆጣጠሩ?

ሁቲዎች በመጀመሪያ ላይ ከፍተኛ ከፍተኛ የፖለቲካ ጥንካሬ ማግኘት የቻሉት ፕሬዚዳንት አሊ አብደላህ ሳሌህን በተኩት በፕሬዚዳንት አብድራቡህ ማንሱር ሃዲ ላይ በተነሱበት ወቅት ነው። ይህም በአውሮፓውያኑ 2014 ወቅት ነው።

ከቀድሞው ጠላታቸው እና ከስልጣን ከተነሱት ፕሬዚዳንት ሳሌህ ጋር ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላም እሳቸውን ወደ ስልጣን ለመመለስ አስበው ነበር።

በቀጣዩ ዓመትም በየመን ሰሜናዊ ክፍል የሚገኘውን የሳዓዳ ግዛትን ተቆጣጠሩ። ይህም ዋና ከተማዋን ሰንዓን መቆጣጠር ያስቻላቸው ሲሆን ፕሬዚዳንት ሃዲንም ወደ ውጭ እንዲሰደዱ አስገደዷቸው።

የየመን ጎረቤት የሆነችው ሳዑዲ አረቢያ ወታደራዊ ጣልቃ በመግባት ፕሬዚዳንት ሃዲን ወደ ስልጣን መለሰች እንዲሁም የሁቲዎችን ኃይልም ለማሸነፍ ሞከረች።

ሳዑዲ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ባህሬንም በመደገፍ ነበር የኃይል ጣልቃ ያደረገችው።

ሁቲዎች የተፈጸመባቸውን ጥቃቶች በመቋቋም ሰፊውን የየመንን ግዛት በመቆጣጠር ቀጥለዋል።

በአውሮፓውያኑ 2017 የቀድሞው ፕሬዚዳንት አሊ አብዱላህ ሳሌህ ወደ ሳዑዲ ጎራ ለመቀላቀል ሲሞክሩም በሁቲ ታጣቂዎች ተገደሉ።

የሁቲ አማጺያን በማን ይደገፋሉ?

የሁቲ አማጺያን በሊባኖስ ውስጥ የሚገኘው የሺአው ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው።

ሄዝቦላህም ለሁቲ አማጽያን ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮም ሰፊ ወታደራዊ ስልጣናዎችን እየሰጣቸው መሆኑን ሽብርተኝነትን የሚዋጋው ‘ዘ ኮምባቲንግ ቴሬሬዚም ሴንተር’ የተሰኘው የአሜሪካው የምርምር ተቋም አስታውቋል።

ሁቲዎች ኢራንን በአጋርነት የሚያይዋት ሲሆን ሳዑዲ አረቢያም የጋራ ጠላታቸው ናት።

ኢራን ለሁቲ አማጺያን የጦር መሳሪያ ታቀርባለችም የሚሉ ጥርጣሬዎችም ጎልተው ይሰማሉ።

ሁቲዎች በአውሮፓውያኑ 2017 በሳዑዲ መዲና ሪያድ ላይ ያስወነጨፉትን ባለስቲክ ሚሳኤል ያቀረበችው ኢራን ናት በማለት አሜሪካ እና ሳዑዲያ አረቢያ ይከሳሉ። ሚሳኤሉ ተተኩሶበት መውደቁ ይታወሳል።

በተጫማሪም በአውሮፓውያኑ 2019 ሁቲዎች የሳዑዲ ነዳጅ ማምረቻዎችን ለማጥቃት የተጠቀሙባቸውን የክሩዝ ሚሳኤሎች እና ድሮኖችን (ሰው አልባ አውሮፕላኖችን) የሰጠችው ኢራን ናት በሚልም ሳዑዲ አረቢያ ትከሳለች።

ሁቲዎች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአጭር ርቀት ሚሳኤሎችን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያስወነጨፉ ሲሆን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኢላማዎችም ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል።

እነዚህን መሳሪያዎች ለሁቲ አማጽያን ማቅረብ የተባበሩት መንግሥታት በኢራን ላይ የጣለውን የጦር መሳሪያ እገዳን የሚጥስ ቢሆንም ኢራን በጭራሽ ክሱን አትቀበለውም።

የሁቲ አማጽያን ያላቸው ኃይል እንዴት ይታያል? የመንንስ ምን ያህል ይቆጣጠራሉ?

በአለም አቀፍ ዕውቅና የተሰጠው መንግሥት የፕሬዚዳንቱ አመራር ምክር ቤት ነው። ፕሬዚዳንት አብዱራቡህ ማንሱር ሃዲ በአውሮፓውያኑ 2022 ስልጣናቸውን ለምክር ቤቱ አስተላልፈውለታል።

ምክር ቤቱ መቀመጫውም በሳዑዲ መዲና ሪያድ ነው። ሆኖም አብዛኛው የየመን ህዝብ የሚኖረው በሁቲ አማጽያን ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች ነው።

ሁቲዎች በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ግብር የሚሰበስቡ ሲሆን የአገሪቱንም መገበያያ ገንዘብም ያትማሉ። የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሁቲዎች በአውሮፓውያኑ 2010፣ ከ100 ሺህ- 200 ሺህ የታጠቁ ወታደሮች እና ያልታጠቁ ደጋፊዎች እንዳላቸው ገልጿል።

ምክር ቤቱ ይህንን መረጃ በሁቲ እንቅስቃሴ ላይ ባለሙያ የሆኑትን አህመድ አል ባህሪን ዋቢ አድርጎም ነው ያሰፈረው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተጨማሪም በየመን ሁቲ አማጽያን የተመለመሉ 1 ሺህ 500 ህጻናት በውጊያ ከሶስት ዓመታት በፊት ሞተዋል ብሏል።

በዓመቱም በመቶዎች የሚቆጠሩ እንደሞቱም ገልጿል።

የሁቲ አማጽያን ሰፊውን የቀይ ባህር ጠረፍ ይቆጣጠራሉ። ከነዚህም አካባቢዎች ነው ጥቃቶቹን እየፈጸሙ የሚገኙት። እነዚህ ጥቃቶች ከሳዑዲ አረቢያ ጋር እያደረጉት ላለው የሰላም ድርድር እንዳገዛቸውም አል ኦሜሲ ያስረዳሉ።

“ለሳዑዲዎች የቀይ ባህር መተላለፊያ የሆነው ባብ አል ማንዳብ መዝጋት እንደሚችሉ በማሳየት ወደ በስምምነቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳረፍ ችለዋል” ይላሉ።