የሩዋንዳ የቀድሞ ፖሊስ በዘር ማጥፋት ወንጀል ፈረንሳይ ውስጥ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት

ፈረንሳይ የሚገኝ ፍርድ ቤት በዘር ማጥፋት ወንጀል በተከሰሰ አንድ የቀድሞ የሩዋንዳ ፖሊስ መኮንን ላይ የዕድሜ ልክ እሥራት ፈረደ።

ሩዋንዳዊው የፖሊስ መኮንን ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት በተፈጸመው የጅምላ ፍጅት ወቅት የዘር ማጥፋት እና በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል መፈፀሙ ተረጋግጧል።

ፊሊፔ ሄትጌኪማና ወንጀሉን የፈፀመው በፈረንጆቹ 1994 በሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ ወቅት ነው።

በወቅቱ የሁቱ ታጣቂዎች በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ቱትሲዎች እና ለዘብተኛ ሁቱዎችን መግደላቸው ይታወሳል።

የፈረንሳይ ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው ግለሰቡ እሱ ራሱ የሰዎችን ነብስ ከማጥፋቱም በላይ ሌሎች ግድያ እንዲፈፅሙ ያነሳሳ ነበር።

ፊሊፔ በጅምላ ግድያው ወቅት ኒያንዛ በተሰኘችው የደቡብ ሩዋንዳ አካባቢ የፖሊስ መኮንን ሆኖ ያገለግል ነበር።

ነገር ግን የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ካቆመ በኋላ ወደ ፈረንሳይ አቅንቶ ለአስርታት ማንነቱ ደብቆ ሲኖር ቆይቷል።

ግለሰቡ ፈረንሳይ ከገባ በኋላ መጀመሪያ የስደተኛ ወረቀት አግኝቶ፤ ቀጥሎ ደግሞ ፊሊፔ ማኒዬ በተሰኘ ስም ዜግነት ተሰጥቶት ኖሯል።

ፈረንሳይ ውስጥ ሳለ የአንድ ዩኒቨርሲቲ ጥበቃ ሆኖ ሲያገልግል ከቆየ በኋላ በአውሮፓውያኑ 2017 ወደ ካሜሩን ያቀናል።

ሰውዬው ይህን ያደረገው አንድ ሰው እሱ ላይ ቅሬታ እንዳለው ድምፁን ካሰማ በኋላ ነው።

ኤኤፍፒ የተባለው የፈረንሳይ ዜና ወኪል እንደዘገበው፣ ፊሊፔ በቁጥጥር ሥር የዋለው በካሜሩኗ ዋና ከተማ ያውንዴ ነው።

ከዚያም ወደ ፈረንሳይ እንዲሄድ ተደርግ የፍርድ ሂደቱን ሲከታተል ቆይቷል።

በሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተሳታፊ ሆነው የተገኙ ግለቦች ፈረንሳይ ውስጥ ፍርድ ሲሰጣቸው ፊሊፔ አምስተኛው ነው።

በሚቀጥለው ዓመት 30ኛ ዓመቱን የሚይዘው እና በ100 ቀናት ውስጥ 800 ሺህ ቱትሲዎች እና ለዘብተኛ ሁቱዎች የተገደሉበት የዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠያቂዎች አሁን ድረስ ጉዳያቸው አልተዘጋም።