ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቡርኪናፋሶ ወታደራዊ መሪዎች የአገሪቱን ምርጫ ኮሚሽን አፈረሱ
የቡርኪናፋሶ ወታደራዊ መሪዎች የአገሪቱን የምርጫ ኮሚሽን የገንዘብ ብክነት ነው በሚል በተኑ።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደፊት የሚደረገውን ምርጫ እንደሚያስተባብር የአገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ አርቲቢ ዘግቧል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2022 መስከረም ወር በመፈንቅለ መንግሥት የአገሪቱን ሥልጣን የተቆጣጠሩት አመራሮች በአገሪቱ የተለያዩ ማሻሻያዎችን ማድረግ ጀምረዋል።
የማሻሻያዎቹ አካል ከሆኑት መካከል ወደ የሲቪል አስተዳደር የሚወስደውን ምርጫ ማራዘምን ያካትታል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ምርጫ መካሄድ የነበረበት ባለፈው ዓመት ቢሆንም ወታደራዊ አመራሮች አገሪቱ ወደ ዲሞክራሲ የምታደርገውን ሽግግር እስከ ሐምሌ 2029 ድረስ አራዝመዋል።
ይህም መሪው ኢብራሂም ትራኦሬ በሥልጣን ላይ እንዲቆዩ እና በሚቀጥለው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ያለ ተቀናቃኝ እንዲወዳደሩ ያስችላቸዋል።
የኤኤፍፒ የዜና ወኪል የጋዝት አስተዳደር ሚኒስትር ኤሚሌ ዜርቦን ጠቅሶ እንደዘገበው የምርጫ ኮሚሽኑ በዓመት 870,000 ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ድጎማ ተደርጎለታል።
ሚኒስትሩ ኮሚሽኑን ማፍረስ "በምርጫ ሂደቱ ላይ ያለንን ሉዓላዊ ቁጥጥር እንደሚያጠናክር እና በተመሳሳይ የውጭ ተጽዕኖዎችን ይገድባል" ብለዋል።
ከሦስት ዓመታት በፊት ወታደራዊ አመራሮቹ ወደ ሥልጣን ሲመጡ የሲቪል ባለስልጣናቱ እየጨመረ የመጣውን እስላማዊ አማጽያን መቋቋም አልቻሉም በሚል ተችተው ነበር።
በወቅቱ የወታደራዊ መሪዎቹ ከቀድሞ ቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ የምትሰጠውን እርዳታ አንቀበልም ሲሉ ውድቅ አድርገዋል።
የመብት ተሟጋቾች ሠራዊቱ ታጣቂዎቹን ለመደምሰስ ባደረገው ሙከራ በሰላማዊ ሰዎች ላይ አነጣጥሯል ሲሉ፣ የፖለቲካ እንቅስቃሴን እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በማፈን ይከስሷቸዋል።
በወታደራዊ ዘመቻው ውጤታማነት ላይ በርካታ ጥያቄዎች ይነሳሉ።
በ2025 የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ የጂሃዲስት ቡድን ጄኤንአይኤም በቡርኪናፋሶ ውስጥ ከ280 በላይ ጥቃቶችን መፈፀሙን ተናግሯል።
ቢቢሲ ባረጋገጠው መረጃ መሰረት ቡድኑ የሚፈጽመው ጥቃት በ2024 ከነበረው በእጥፍ አድጓል።
እ.ኤ.አ. በ 2022 በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ፣ የትራኦሬ አገዛዝ የቀድሞ የቡርኪናፋሶን ቅኝ ገዢ ፈረንሳይን ምትክ ከሩሲያ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት እንድትመሠርት አድርጓል።