ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ 1200 ስደተኞች ጣሊያን ደሴት ደረሱ
የጣሊያን መንግሥት ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ ወደ 1 ሺህ 200 የሚጠጉ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች ጣሊያን መግባታቸውን ገለፁ።
ከተለያዩ የእስያ፣ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የተውጣጡ ስደተኞች ሲሲሊ ወደቦች በጀልባዎች ተጭነው ደርሰዋል።
ባሳላፍነው ቅዳሜ እና እሁድ ወደ ጣሉያን የገቡት ስደተኞች ከአፍጋኒስታን፣ ፓኪስታን፣ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የመጡ መሆናቸውን በነፍስ አድን ተግባር ላይ የተሰማሩት ሰዎች ገልጸዋል።
ባለስልጣናቱ እንዳሉት በካላብሪያ የባህር ዳርቻ ብቻ 674 ሰዎችን የተቀበሉ ሲሆን፤ አምስት አስከሬኖችም ከስደተኞቹ ጋር በሰው በተጨናነቁት የአሳ ማጥመጃ ጀልባዎች ላይ ተጭነው ተገኝተዋል።
እንዲሁም በ15 ጀልባዎች ተጭነው የመጡ 522 ስደተኞች ባሳለፈነው ቅዳሜ ወደ ላምፔዱሳ ወደብ ደርሰዋል።
ከሊቢያ እና ቱኒዚያ የተነሱት ጀልባዎች ወደ አውሮፓ ለመግባት የሚፈልጉ ሰዎች መዳረሻ ከሚያደርጓቸው ወደቦች መካከል አንዱ ወደ ሆነው ላምፔዱሳ ደርሰዋል።
የጣሊያን መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት በሲሲሊ ደሴት የሚገኘው የስደተኞች ማዕከል ማረፊያዎች ባለፉት ሳምንታት ውስጥ በከፍተኛ መጠን ተጨናንቋል።
ማዕከሉ ከሚችለው የ350 ሰዎች አቅም በላይ በአሁኑ ጊዜ 1 ሺህ 184 ሰዎችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል።
የባህር ዳርቻ ጥበቃ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ስደተኞችን ከባሕር ላይ ይታደጋሉ።
የሜዲትራኒያን ባሕር ለሕገ-ወጥ ፍልሰት በጣም አደገኛ ከሆኑ መንገዶች አንዱ ነው።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ከሆነ እ.ኤ.አ በ2021 በሜዲትራኒያን ባሕር እና በሰሜን ምዕራብ አትላንቲክ ውቅያኖስ ውስጥ ከ3ሺህ 200 በላይ ሰዎች ሞተው ወይም ጠፍተዋል ተብለው ተመዝግበዋል።
አደገኛውን ጉዞ ከሚያደርጉት መካከል ብዙዎቹ ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በሚያቀርቡላቸው ጊዜያዊ ጀልባዎች ላይ የሚሳፈሩ ሲሆን ጀልባዎቹ በጉዞ መሃል ስራውቸውን በሚያቆሙበት ወቅት ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎቹ ስደተኞቹን ባሕር ላይ ትተዋቸው ይሄዳሉ።