ኮሎምቢያዊው አደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን መሪ አሜሪካ ውስጥ የ45 ዓመት እሥር ተፈረደበት

የአሜሪካ ፍርድ ቤት ዳይሮ አንቶኒዮ ኡሱጋ የተባለውን በአንድ ወቅት በኮሎምቢያ እጅግ ተፈላጊ የነበረውን ግለሰብ ላይ የ45 ዓመት እሥር በየነበት።

ኦቶኒዬል በተሰኘ ቅፅል ስሙ የሚታወቀው ኡሱጋ ለዘጠኝ ዓመት የኮሎምቢያ ዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን መሪ ነበር።

ግለሰቡ ባለፈው ጥር የወንጀለኛ ቡድን መምራትን ዕፅ ማዘዋወር በሚሉ ክሶች ጥፈተኛ መሆኑን አምኗል።

ማክሰኞ ዕለት ፍርዱን የተቀበለው ኡሱጋ ለፈፀመው ወንጀል ይቅርታ ጠይቋል።

“ለዩናይትድ ስቴትስ እና ለኮሎምቢያ መንግሥታት ይቅርታዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ። በፈፀምኩት ወንጀል ሰለባ ለሆኑም ይቅርታ እጠይቃሁ” ብሏል የ51 ዓመቱ ግለሰብ።

አቃቤ ሕግ ግለሰቡን “ከማዴይን ዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን መሪ ፓብሎ ኤስኮባር ቀጥሎ ትልቁ የኮሎምቢያ ዕፅ አዘዋዋሪ” ብለውታል።

የአሜሪካ ዕፅ ቁጥጥር ባለሥልጣን “በዓለማችን ካሉ እጅግ አደገኛ ዕፅ አዋዋሪዎች መካከል አንዱ ነው” ይለዋል።

ኡሱጋ በፈረንጆቹ 2021 በቁጥጥር ሥር ውሎ በፅዕ ዝውውር ክስ ወደ አሜሪካ እንዲዘዋቀወር ተደርጓል።

የግለሰቡ ጠበቃዎች ደንበኛቸው ከ25 ዓመታት እሥር ያልዘለለ ቅጣት እንዲሰጠው ለማድረግ ሞክረው ነበር።

በድኅነት እና በደፈጣ ውጊያ ተከቦ ማደጉ ወደ ወንጀል ሕይወት እንዲያመራ አድርጎታል ሲሉም ሞግተዋል።

ነገር ግን ጉዳዩን ይዘውት የነበሩት ዳኛ ዶራ ኢሪዛሪ ደቡብ ብሮንክስ በተሰኘው አካባቢ በዕፅና አመፅ ተከበው ቢያድጉም ወንጀለኛ ሳይሆኑ ለዚህ እንደበቁ በመናገር የጠበቆቹን ሙግት ውድቅ አድርገውታል።

ወንጀለኛ መሆኑን ያመነው ኡሱጋ ከዕፅ ንግድ ያገኘውን 216 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ለመንግሥት ገቢ አድርጓል።

በኮሎምቢያ ገልፍ ክላን የተሰኘው ዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን መሪ የነበረው በሃገሪቱ እጅግ ጨካኝ ከሚባሉ ቡድኖች መካከል በቁንጮነት ይመደብ ነበር።

የኮሎምቢያ ፀጥታ አካላት ይህን የዕፅ አዘዋዋሪዎች ቡድን በአገሪቱ ያለ አደገኛ የወንጀለኛ ቡድን ሲሉ ፈርጀውት ነበር።

የአሜሪካ መንግሥት ደግሞ ይህ ቡድን "እስከ አፍንጫው የታጠቀ እና እጅግ አመፀኛ" ሲል ይፈርጀዋል።

ቡድኑ 1800 የሚሆኑ የታጠቁ አባላት እንዳሉት፤ እኒህ አባላት ደግሞ የቀኝ ዘመም አስተሳሰብ አራማጆች እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።

የዚህ ቡድን አባላት የሆኑ ሰዎች ከዚህ ቀደም ብራዚል፣ አርጀንቲና፣ ሆንዱራስ፣ ፔሩና ስፔን ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

በኮሎምቢያ አብዛኛው ክፍል እጁ ይዘረጋ የነበረው ኡሱጋ በዓለም አቀፍ ደረጃም ከተለያዩ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ነበረው።

ከዕፅ ዝውውር በተጨማሪ በሕገ-ወጥ መንገድ ሰዎችን በማዘዋወር እንዲሁም ሕጋዊ ባለሆነ መንገድ ወርቅ በመቆፈርም ተሰማርቶ ነበር።

ከኮሎምቢያ ወደ አሜሪካ የሚጓዝ የትኛውም ዓይነት ዕፅ ከሱ ቁጥጥር ውጭ አይሄድም።

ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ሳይሆን እስከ ሩሲያ ድረስ የሚጓ ዕፅ ከኡሱጋ ቡድን እውቅና ውጭ አይጓዝም ነበር።