ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩናይትድ አየር መንገድ አውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ 200 ሚሊዮን ዶላር አሳጣኝ አለ
የአሜሪካው ዩናይትድ አየር መንገድ አውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ በባለፉት ሦስት ወራት 200 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አሳጣኝ አለ።
አየር መንገዱ ማግኘት የነበረብኝን 200 ሚሊዮን ዶላር ያጣሁት ቦይንግ 737 ማክስ 9 አውሮፕላኖችን ከበረራ አግጄ በማቆየቴ ነው ብሏል።
ከጥቂት ወራት በፊት ንብረትነቱ የአላስካ አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ ሰራሹ 737 ማክስ 9 አውሮፕላን በረራ ላይ ሳለ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሩ ተገንጥሎ መውደቁ ይታወሳል።
ይህን አደገኛ ክስተት ተከትሎ ዩናይትድ አየር መንገድ 79 ማክስ 9 አውሮፕላኖቹን ለተሳፋሪዎቹ ደኅንነት ሲል ከበረራ ለማገድ ተገዶ ነበር።
የአሜሪካ የበረራ ደኅንነት ተቆጣጣሪዎች የአደጋ ጊዜ መውጫ በሩ እንዴት ተገንጥሎ ሊወድቅ እንደቻላ የሚያደርጉትን ማጣራት እስኪጨርሱ ድረስ ዩናይትድ እና አላስካ ማክስ 9 አውሮፕላኖችን ከበረራ በማስወጣታቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ በረራዎችን ለመሰረዝ ተገደዋል።
የአላሳካው 737 ማክስ 9 አውሮፕላን በረራ ላይ ሳለ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሩ የተገነጠለው የአደጋ ጊዜ መውጫ በሩን አስረው መያዝ የነበረባቸው አራት ብሎኖች በቦታቸው ስላልነበሩ ነው መባሉ ይታወሳል።
የአሜሪካ ብሔራዊ የትራንስፖርት ደኅንነት ቦርድ ክስተቱን ምርምሮ ሪፖርቱን ካወጣ በኋላ ቦይንግ ለችግሩ ተጠያቂው እኔ ነኝ ብሎ ነበር።
የአላስካው 737 ማክስ 9 አውሮፕላን ለበረራ ከተነሳ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሩ ከተገነጠለ በኋላ በተሳፋሪዎች ላይ ምንም ጉዳት ሳይደርስ በአስቸኳይ ማረፍ ችሎ ነበር።
ክስተቱን ተከትሎ 737 ማክስ 9 አውሮፕላን በመላው ዓለም ከበረራ ታግዶ እንዲቆይ ተደርጓል።
737 ማክስ 9 አውሮፕላን ላይ ያጋጠመውን ክስተት የመረመረው የአሜሪካው ብሔራዊ የትራንስፖርት ደኅንነት ቦርድ የተገነጠለው በር የተሰራው የቦይንግ አቅራቢ በሆነው ስፒሪት ኤየሮሲስተምስ ነው ብሏል።
ስፒሪት ኤየሮሲስተምስ በሩን የአውሮፕላኑ አካል ላይ ገጥሞ ቢያስረክብም ቦይንግ ደርሶ በምርት ሂደት ላይ ችግር ተገኝቶ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሩ እንዲፈታ ተደርጎ ተመልሶ ሲገጠም አራት ብሎኖች ጎድለዋል።
ቀደም ሲል ቦይንግ ለአላስካ አየር መንገድ 160 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ከፍሎታል።
ከዓለም ቀዳሚ አየር መንገዶች መካከል አንዱ የሆነው ዩናይትድ ማክስ 9 ካሳጣኝ ገቢ በተጨማሪ ቦይንግ የታዘዘውን ሌሎች አውሮፕላኖች በፍጥነት ማስረከብ ባለመቻሉ በሥራዬ ላይ መስተጓጎል ተፈጥሯል ብሏል።