አርሰናል ከጥቁር ማንነት ጋር እንዴት ሊተሳሰር ቻለ?

ዶ/ር ክላይቭ ቺጂዮኬ ንዎንካ በአውሮፓውያኑ መስከረም 28 ቀን 2002 ከጓደኞቻቸው ጋር ለመገናኘት ማንቸስተር ውስጥ ወደሚገኝ ቡና ቤት በቀጠሯቸው ሰዓት ደረሱ። ምንም የተለየ ነገር ያለ አይመስልም።

ሆኖም የእግር ኳስ እና የባህል ታሪክ ሊመለከቱ ነበር።

በዕለቱ አርሰናል ዘጠኝ ጥቁር ተጫዋቾችን በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ በማካተት የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያው ቡድን ሆነ።

መድፈኞቹ ከሜዳቸው ውጪ ሊድስ ዩናይትድን 4 ለ 1 ሲያሸንፉ ቲየሪ ኦንሪ፣ ንዋንኮ ካኑ እና ኮሎ ቱሬ ኳስ እና መረብ አገናኝተዋል።

በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ንዎንካ “ብቃታቸው የዚህን ታሪካዊ እና በማንነት ላይ ያለውን ተጽዕኖ ከፍ አድርጎታል” ሲሉ ለቢቢሲ አፍሪካ ተናግረዋል።

“ይህንን ያሳኩትም በቃታቸው መሆኑ ትክክለኛነቱን አስመስክሯል።”

ዶ/ር ንዎንካ ክለቡ ለጥቁሮች ባህላዊ ታሪክ ያበረከተው አስተዋፅኦ በቅርቡ ለህትመት በበቃው “ብላክ አርሰናል” በተሰኘው እና በተባባሪ አርታኢነት በተሳተፉበት መጽሐፍ ላይ ተካቷል። ከሰሜን ለንደኑ ክለብ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ምስክርነቶችን እና ፎቶግራፎችንም አካትተዋል።

“እኔ ብሪቲሽ ናይጄሪያዊ ነኝ። ጥቁር በተለይም አፍሪካውያን ተጫዋቾችን በብሪቲሽ እግር ኳስ ተወክለው ማየት ለእኔ ትልቅ ነገር ነው” ብለዋል።

በመጽሐፉ አርሰናል በፕሪምየር ሊጉ ጥቁር ተጫዋቾች ይበልጥ እንዲጫወቱ እና በኤምሬትስ ስታዲየም የጥቁር ሴት ደጋፊዎች ቁጥር እየጨነረ እንዲመጣ የተደረገው ጥረት ተተንትኗል።

“ብዙም ጥናት ባይደረግበትም፤ ጥቁሮች ከአርሰናል ጋር ስላላቸው ግንኙነት በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር እንዳለ ሁልጊዜም ይሰማኝ ነበር” ብለዋል ዶ/ር ንዎንካ።

የቡድኑ የልብ ደጋፊዎቻቸው ለክለባቸው የሚሰጡት ድጋፍ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው መቀጠሉን የሚያሳይ ቁርጠኝነትም በመጽሐፉ ውስጥ ተንጸባርቋል።

“አርሰናል ስል ለጥቁሮች የአርሰናል ባህል ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ መግለጼ ነው” ሲሉ ዶ/ር ንዎንካ አክለዋል።

“ክለብ ሲባል ጡብ እና ስሚንቶ ማለት ሳይሆን አርሰናል በጥቁሮች ባህል ውስጥ የሚጠቀስባቸው ናቸው። ይህ ደግሞ በሥራ ቦታ፣ ፀጉር ማስተካከያዎች እና በቤተ እምነቶች ሊሆን ይችላል።”

ቬንገር እና አፍሪካ

ኢያን ራይት በአውሮፓውያኑ በ1990ዎቹ ውስጥ ላደጉ ብዙ ጥቁር የአርሰናል ደጋፊዎች ምልክት ሆኖ ይታያል። የወርቅ ጥርሱ፣ የግራመ ሞገሱ፣ ስብዕና እና የጎል ረሃቡ ይጠቀሳሉ።

በጥቁር አርሰናል ተጫዋቾች ማሳያነት ቢነሳ ብዙ የመድፈኞቹ ደጋፊዎች አይቃወሙትም። ለዶ/ር ንዎንካ እና ለሌሎች ናይጄሪያውያን ግን ሌላ ኮከብ ተጫዋች ቀድሞ ያነሳል።

እአአ በ1996 አርጀንቲናን አሸንፎ የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳልያ ያገኘውን የናይጄሪያ የኦሊምፒክ እግር ኳስ ቡድን አይዘነጋም። በተለይም ብራዚልን በግማሽ ፍጻሜው ሲያሸንፉ ወሳኙን ግብ ያስቆጠረው ሰው ቀድሞ ብቅ ይላል - ንዋንኮዎ ካኑ።

በኢሞ ግዛት የተወለደው አጥቂው በአውሮፓውያኑ 1999 ነበር ከጣሊያኑ ኢንተር ሚላን አርሰናልን የተቀላቀለው።

“እርሱ አርሰናልን መቀላቀሉ ለእኔ እና እንደ እኔ ላሉ ሰዎች ልዩ ባህላዊ ጠቀሜታ ነበረው” ብለዋል ዶ/ር ንዎንካ።

በወቅቱ የአርሰናል አሠልጣኝ የነበሩት አርሰን ቬንገር ከ1996 እስከ 2018 በቆዩባቸው 22 ዓመታት የአፍሪካ እና የፈረንሳይ ኮከብ ተጫዋቾችን በማስፈረም ይታወቃሉ።

ቡድኑ ሲደክም የእንግሊዝ ታብሎይድ ጋዚጦች ስም ያላቸው እና የእንግሊዝን ሊግ የሚያውቁ ተጫዋቾችን ማስፈረም አለባቸው እየተባሉ ይብጠለጠሉ ነበር።

ፈረንሳዊው አሠልጣኝ አርሰናልን በ2003-04 የውድድር ዓመት የሊጉን ዋንጫ እንዲያሸንፍ ሲረዱ ትልቅ ክብር ተቸራቸው።

ዋንጫ ብቻ አልነበረም ያገኙት። የቬንገር ቡድን አንድም ጨዋታ አልተሸነፈም። ይህ ታሪክ ሊደገም አልተቻለም።

ይህ ቡድን የአይቮሪ ኮስቱን ተከላካይ ኮሎ ቱሬ፣ ካሜሮኑን የቀኝ መስመር ተከላካይ ላውረንን እና ካኑን አካቷል።

“ጥሩ የሚጫወቱ እና የሚያዝናኑ የአፍሪካ ተጫዋቾች መኖራቸው አንድ ነገር ነው። በእነዚህ ተጫዋቾች ማሸነፍ ደግሞ ለውጥ ያመጣል” ብለዋል ዶ/ር ንዎንካ።

ይህን የስኬት ሞዴል የተከተለው የለንደን ተቀናቃኙ ቼልሲ በአሠልጣኝ ሆዜ ሞሪንሆ ስር ውጤታማ ሆኖበታል። የአይቮሪኮስቱ ዲዲየ ድሮግባ፣ የጋናው ማይክል ኢሲየን እና ናይጄሪያዊው ጆን ኦቢ ሚኬል ተጠቃሾቹ ተጫዋቾች ናቸው።

ዘረኝነትን መዋጋት

ጥቁር እግር ኳስ ተጫዋቾች አስደናቂ ስኬት ቢያስመዘግቡም ዘረኝነት ግን ሜዳው ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ውጭም ተከትሏቸዋል።

እንግሊዝ በዩሮ 2020 የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ በጣሊያን ተሸንፋለች። ሽንፈቱን ተከትሎ ቡካዮ ሳካ፣ ጃደን ሳንቾ እና ማርከስ ራሽፎርድ በጨዋታው የመለያ ምት በመሳታቸው በበይነ መረብ ላይ የዘረኝነት ጥቃት አስተናግደዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም 11 ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፣ አርሰናል ለሳካ እና ለሦስቱ አናብስት የቡድን አጋሮቹ የድጋፍ መግለጫ አውጥቷል።

“ይህ ሊቀጥል አይችልም። የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች እና ባለሥልጣናት ተጫዋቾቻችን በየቀኑ የሚደርስባቸውን አጸያፊ ጥቃት በፍጥነት መቆሙን ለማረጋገጥ እርምጃ መውሰድ አለባቸው” ብሏል።

ሳካ ላይ የሚደርሰው ጥቃት አልተቋረጠም። ባለፈው ዓመት በኖቲንግሃም ፎረስት ከተሸነፉ በኋላም ጥቃት ተሰንዝሮበታል።

በዚህ የውድድር ዘመን በሁሉም የእንግሊዝ የእግር ኳስ እርከኖች በብዛት ተመዘገበው የመድልዎ ዓይነት ዘረኝነት እንደሆነ በፀረ-መድልዎ ላይ የሚሠራው “ኪክ ኢት አውት” ያሰባሰበው መረጃ ያሳያል።

ከአናሳ ማኅበረሰቦች የመጡ ተጫዋቾች በበይነ መረብ ዒላማ ይደረጋሉ። በሚወክሉት ብሔራዊ ቡድን አገር ተወልደው ቢያድጉም የሕብረተሰቡ አካል እንዳልሆኑ ይነገራቸዋል።

የዘር ጥላቻ ጥቁር ተጫዋቾችን ለመግለጽ በሚጠቀሙበት ቋንቋም የተጠናከረ ነው ብለው ዶ/ር ንዎንካ ያስባሉ። “በዘር የተከፋፈለ፣ የሚያገል፣ አሉታዊ እና አላዋቂ” ሆነውም ያገኟቸዋል።

ጥቁር እና ነጭ ስፖርተኞች የዘረኝነት ጉዳይ ላይ ሁለት የኔዘርላንድ ዩኒቨርሲቲዎች በቅርቡ ባደረጉት ጥናት ይህንን ምልከታ አስተጋብተውታል።

በዩትሬች ዩኒቨርሲቲ እና በሮተርዳም ኢራስመስ ዩኒቨርስቲ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ “ነጭ [ስፖርተኞች] ብዙውን ጊዜ በእውቀት የላቁ እና ታታሪ እንደሆኑ ተደርገው በማኅበረሰቡ ውስጥ ይሳላሉ። ጥቁር ስፖርተኞች ደግሞ ከአካላዊ ጥንካሬ እና ከተፈጥሮ ጋር በተቆራኘ አካላዊ ጥንካሬያቸው ምክንያት በስፖርቱ የላቀ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ይታሰባል” ብሏል።

የአርሰናል የወደፊት ዕጣ ፈንታ

በዘንድሮው የውድድር ዓመት አርሰናል ከአፍሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት ለመዘከር በሚል ከሜዳው ውጪ የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች ከፓን አፍሪካ ባንዲራ በተወሰዱ ቀለማት ባሸበቀረ መለያ ይጫወታል።

በሴራሊዮን የተወለደው ፎዳይ ዱምቡያ ማሊያውን ነድፎታል። ይፋዊ ማስታወቂያው የተቀረጸው በአገሪቱ ርዕሰ መዲና ፍሪታውን ነው።

“ወደ መጣሁበት መመለስ ጥሩ ነው። ልጆች ከእግር ኳስ ጋር የሚገናኙበትን መንገድ እና በአፍሪካ እግር ኳስ የሚታይበትን መንገድ መመልከት መልካም ነው። ምክንያቱም እግር ኳስ ሕይወት ነው” ሲል ዱምቡያ ተናግሯል።

ለንደን ያደጉት ዶ/ር ንዎንካ በበኩላቸው የአርሰናልን መለያ የከተማዋ ዩኒፎርም ሲሉ ገልፀውታል።

በአፍሪካ ተመሳሳይ ዝንባሌ እንደሚንጸባረቅ ይሰማቸዋል።

ከናይጄሪያውያን ወላጆች በለንደን የተወለደው ሳካ በአርሰናል ደጋፊዎች “ኮከብ ልጅ” ተብሎ ይመለካል። ለወጣት እና ታዋቂ ሰው የሚሰጥ ስያሜ ነው። ከሜዳው ውጪ የሚጫወቱበትን መለያ ካስተዋወቁት መካከልም አንዱ ነበር።

የ23 ዓመቱ ተጫዋች ለመድፈኞቹ ከ230 በላይ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፏል። እግር ኳስ ውስጥ ያለውን ዘረኝነትን እና የባህል ስሱነት በመዋጋት ላይ መሆኑንም ተናግሯል።

“እሱም ከዘርም በላይ ነው። ብሪቲሽ እና ናይጄሪያዊ በመሆኑ የተሻጋሪ ባህል ፍላጎት አለው” ብለዋል ዶ/ር ንዎንካ።

ኮከቡ ተጫዋች ለክለቡ ብቻ ሳይሆን ለብሔራዊ ቡድኑም በቋሚነት ይሰለፋል። የኋላ ታሪካቸው ምንም ይሁን ምን ለቀጣዮቹ የእግር ኳስ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች ምሳሌ ነው።

በአርሰናል እና በጥቁር ተጫዋቾች መካከል ያለውን ትሰስር የሚያሳይ የዘመኑ ተጫዋች ነው።