የደቡብ አፍሪካ የፖሊስ ሚኒስትር በተደራጀ የወንጀል ድርጊት ተጠርጥረው ከስልጣን ታገዱ

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ፤ ከተደራጀ የወንጀል ድርጊት ጋር ግንኙነት አላቸው የሚል ውንጀላ የቀረበባቸውን የአገሪቱን የፖሊስ ሚኒስትር ሴንዞ ሙቹኑን በአስቸኳይ "እረፍት" አስወጡ።

ራማፎሳ፤ እሁድ ዕለት በቴሌቪዥን ቀጥታ በተላለፈ እና ለአገሪቱ ዜጎች ባደረጉት ንግግር፤ ክሶቹን ሕገ መንግሥቱን የሚያዳክሙ እና ብሔራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ሲሉ የገለጿቸው ሲሆን ጉዳዩ በፍትህ ኮሚሽን እንደሚታይ አስታውቀዋል።

የሕግ ፕሮፌሰር የሆኑ ፊሮዝ ካቻሊያ ጊዜያዊ የፖሊስ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውንም ይፋ አድርገዋል።

ሙቹኑ በበኩላቸው ምንም ዓይነት ጥፋት አለመፈጸማቸውን በመግለጽ "ለቀረቡባቸው ክሶች ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።

በሙቹኑ ላይ ከቀረቡት ክሶች መካከል የፖለቲካዊ ግድያዎች በተመለከቱ ምርመራዎች ውስጥ ጣልቃ መግባትን እና ከሕግ አስፈጻሚ ኤጀንሲዎች ጋር የተያያዙ የሙስና ድርጊቶች ይገኙበታል።

ፕሬዚዳንቱ በትናንቱ ንግግራቸው፤ በሙቹኑ ላይ የቀረቡት ክሶች "አስቸኳይ እና አጠቃላይ ምርመራን እንዲደረግ" ጥሪ አቅርበዋል።

በአገሪቱ ምክትል ዋና ዳኛ የሚመራው የፍትህ ኮሚሽን ሁሉንም ውንጀላዎች እንደሚመረምር ተናግረዋል።

በተጨማሪም ኮሚሽኑ በሥልጣን ላይ ያሉ እና የቀድሞ የፖሊስ ባለስልጣናት እንዲሁም የብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ አባላትንም ይመረምራል ብለዋል።

ራማፎሳ በከፍተኛ እውቅና ባላቸው ውንጀላዎች ላይ በፍጥነት እርምጃ እንዲወስዱ የሚደረገው ሕዝባዊ ጫና እየጨመረ መጥቷል።

የ67 ዓመቱ ሙቹኑ፤ በራማፎሳ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ፓርቲ ውስጥ ተደማጭነት ያላቸው ግለሰብ ናቸው።

የፖለቲካ ተንታኞች በ2027 በሚካሄደው የኤኤንሲ ኮንፈረንስ ላይ ለአመራር ቦታ ሊወዳደሩ እንደሚችሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ሙቹኑ ባወጡት መግለጫ፤ "የፕሬዝዳንቱን ውሳኔ በደስታ እቀበላለሁ እንዲሁም አከብራለሁ፤ ለሂደቱም ያለኝን ቁርጠኝነት ቃል እገባለሁ" ብለዋል።

"ክብር እና ታማኝነት እኔ በግሌ የምደግፋቸው እና ሁላችንም ጥረቶችን ልንጠብቃቸው የሚገኑ እሴቶች ናቸው" ሲሉም አክለዋል።

ባለፈው እሁድ ለመጀመሪያ ጊዜ ክሱ ይፋ የተደረገው የኳዙሉ ናታል ክልል የፖሊስ አዛዥ በሆኑት እንካንክላ ምክዋናዚ ነው። የፖለስ አዛዡ፤ ማቹኑ "የፖለቲካ ጥረቶቹን" ለመደገፍ ከሙሰኛ ነጋዴ የገንዘብ ድጋፍ እያገኙ ነው በማለት ወንጅለዋል።

ሌፍተናንት ጄኔራል ምክዋናዚ፤ በተለይም በኳዙሉ-ናታል ውስጥ የተፈጸ የፖለቲከኞችን ግድያ ለመመርመር በ2018 የተቋቋመው ግብረ ኃይል እንዴት "በተቀናጀ መንገድ" እንዲፈርስ እንዳደረጉ በቅደም ተከተል ዘርዝረዋል።

የግበረ ኃይሉ ምርመራዎች ፖለቲከኞች፣ የፖሊስ ባለስልጣናት እና ከአደንዛዥ እፅ ካርቴል ጋር የተያያዙ ነጋዴዎችን ጨምሮ ከፍተኛ እውቅና ያላቸው ግለሰቦች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው እንደደረሰበት ገልጸዋል። ቡድኑ እንዲበተን የተደረገውም በዚህም ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል።

ሙቹኑ በዚህ ዓመት መጀመሪያ የምርመራ ግብረ ኃይሉ እንዲፈርስ ሲያደርጉ ቡድኑ ለክልሉ ምንም ነገር እየጨመረ አይደለም ብለው የነበረ ቢሆንም በወቅቱ በርካታ ያልተፈቱ ጉዳዮች ነበሩ።

ጄኔራል ማክዋናዚ እንደሚናገሩት፤ በሚኒስትሩ ትዕዛዝ 121 ሰነዶች ከቡድኑ እጅ እንዲወጣ ተደርጓል። ይህ የሚኒስትሩ ትዕዛዝ የተለላለፈው የበላይ ኃላፊ የሆኑት የብሄራዊ ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ፋኒ ማሴሞላን ፈቃድ ሳያገኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ጄኔራል ማክዋናዚ፤ "እነዚህ የክስ መዝገቦች ከመጋቢት ወር ጀምሮ ምንም ዓይነት የምርመራ ሥራ ሳይሰራባቸው በዋናው ቢሮ ውስጥ ተቀምጠዋል። ከእነዚህ መዝገቦች ውስጥ አምስቱ ቀድሞውኑ እስር [እንዲፈጸም] ትዕዛዝ የተሰጠባቸው ናቸው" ብለዋል።

ሚንስትሩ የፖለቲካ ጉዟቸውን በገንዘብ ከሚደግፍ አወዛጋቢ ነጋዴ ጋር ግንኙነት እንዳላቸውም በመጥቀስ ክስሰዋል።