ደቡብ አፍሪካዊው ፖለቲከኛ ጁሊየስ ማሌማ ወደ ዩኬ እንዳይገባ ተከለከለ

አወዛጋቢው እና በዘር ተኮር ጉዳዮች ላይ በሚደረጉ ክርክሮች ስሙ የሚነሳው የደቡብ አፍሪካ ፖለቲከኛ ጁሊየስ ማሌማ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እንዳይገባ ተከለከለ።

ፖለቲከኛው ጁሊየስ ማሌማ "ለህዝብ ጥቅም ግልጋሎት የሌለው" የሚል ብያኔ እንደተሰጠው የገለጸው የዩኬ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር፤ በዚህም ምክንያት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ መፍቀድን "አላስፈላጊ" ሆኖ እንዳገኘው ገልጿል።

ኒውስ 24 በተሰኘው የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የታተመው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፤ የዩናይትድ ኪንግድም መንግሥት ፖለቲከኛው ለሀማስ ያለውን ከፍተኛ ድጋፍ ጠቅሷል።

ማሌማ ከመስከረም 26ቱ የሀማስ ጥቃት ባደረገ ንግግር፤ ሀማስ ወደ ስልጣን የሚመጣ ከሆነ እርሱ እና ፖለቲካ ፓርቲው ቡድኑን እንደሚያስታጥቁ መግለጹም በደብዳቤው ላይ ተካትቷል።

የዩኬ መንግሥት ፖለቲከኛው ወደ ሀገር እንዳይገባ ለማድረጉ በስጋትነት የጠቀሰው ሌላኛው ምክንያት "ነጭ ሰዎች እንዲታረዱ" እንዲሁም ሰዎች "መሳሪያ እንዲያነሱ" ጥሪ አድርጓል የሚል ነው።

'ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ' የተሰኘው እና ባለፈው ዓመት በተካሄደው የደቡብ አፍሪካ ፓርላማ ምርጫ አራተኛ ደረጃን ያዘው የፖለቲከኛው የፖለቲካ ፓርቲ፤ "ፈሪነት" ነው ሲል ውሳኔውን ተቃውሟል።

ውሳኔው ዴሞክራሲያዊ ክርክርን ያፍናል ሲልም ተችቷል።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ባለፈው ወር በአሜሪካ ዋይት ሀውስ በተገኙበት ወቅት፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፖለቲከኛው ማሌማ የሚታይበት አንድ ቪዲዮ እንዲታይ አድርገው ነበር።

ማሌማ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እንዳይገባ ሲከለከል በሁለት ወራት ውስጥ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

የዩኬ መንግስት በመጀመሪያው ዙር ፖለቲከኛው ወደ ሀገር እንዳይገባ የከለከለው ጥያቄው ዘግይቶ በመቅረቡ እንደሆነ ገልጾ ነበር።

በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ አንድ የብሪታኒያ ባለስልጣን የአሁኑ ክልከላ "ጠቃሚ ውሳኔ" እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግስት፤ ማሌማ በውሳኔው ላይ ይግባኝ የመጠየቅ መብት እንደሌለው እንዲሁም ወደፊትም ወደ ሀገሪቱ ለመግባት የሚያቀርበው ጥያቄ ውድቅ ሊደረግ እንደሚችል መግለጹን ኒውስ 24 ዘግቧል።