በቀን ስምንት ብርጭቆ ውሃ መጠጣት ብዙ ሊሆን እንደሚችል አንድ ጥናት አመለከተ

አንድ ሰው በቀን ስምንት ብርጭቆ ውሃ መጠጣት እንዳለበት ሲሰጥ የነበረው የጤና ምክር ከሚያስፈልገው በላይ ሊሆን ይችላል ሲል አንድ ጥናት አመለከተ።

የአበርዲን ዩኒቨርስቲ ሳይንቲስቶች በቀን ሁለት ሊትር ውሃ እንዲጠጣ ሲመከር የቆየው ሃሳብ አንድ ሰው ከሚያስፈልገው በላይ እንደሚሆን በጥናት እንደደረሱበት ገልጸዋል።

አንድ ሰው በቀን ማግኘት ከሚገባው የውሃ መጠን ውስጥ ግማሽ ያህሉን ከምግብ ማግኘት ስለሚችል፣ በቀን መጠጣት ያለበት ውሃ ከ1.5 አስከ 1.8 ሊትር ያልበለጠ መሆን እንዳለበት ተመራማሪዎቹ መክረዋል።

ይህ የሳይንቲስቶቹ የጥናት ግኝት ‘ሳይንስ’ በተባለው የምርምር መጽሔት ላይ በዚህ ሳምንት ይፋ ሆኗል።

አንድ ሰው በቀን የሚያስፈልገውን የውሃ መጠን ለማወቅ ከዚህ ቀደም የተደረገው ጥናት የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን እንደናሙና በመውሰድ የተሰራ ነው።

የአበርዲን ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ጆን ስፒክማን ለቢቢሲ ሬዲዮ እንደተናገሩት “በመጀመሪያ አንድ ሰው በቀን ሁለት ሊትር ውሃ መጠጣት እንዳለበት ሲመከር የተወሰነ የስሌት ስህተት ነበረበት።

“መጠጣን ያለብን የውሃ መጠን መሆን ያለበት ከምንመገባቸው ምግቦች ከምናገኘው ውሃ የተረፈውን መሆን አለበት። ይህ ስሌታቸው ደግሞ መሠረት ያደረገው ሰዎች ምን ያህል ምግብ እንደሚበሉ በመጠየቅ ላይ ብቻ ስለነበር ስህተት ነበረው።”

በጥናቱ ወቅት ሰዎች የሚመገቡትን የምግብ መጠን ዝቅ አድርገው በመናገራቸው፣ አንድ ሰው መጠጣት ያለበትን የውሃ መጠን ከሚገባው በላይ እንዲገመት አድርጎታል ብለዋል።

አሁን ግን አጥኚዎቹ ጥናቱ የተደረገባቸውን ሰዎች ቁጥር ከፍ በማድረግና በትክክል የሚያስፈልጋቸውን ውሃ ለማወቅ የሚያስችል አስተማማኝ ዘዴን መጠቀማቸው ተገልጿል።

በጥናቱ ከ23 የተለያዩ የዓለም አገራት 5,604 ሰዎች የተካተቱ ሲሆን፣ ከዕድሜ አንጻርም ከስምንት ቀን አስከ 96 ዓመት የሚደርሱ ሰዎች ተካተውበታል።

በጥናቱ ውስጥ በውሃ ውስጥ ያሉ ይዘቶች፣ ሰዎች የሚኖሩባቸው አካባቢዎች የአየር ሁኔታ፣ ጾታ፣ እድሜ እና ሌሎች የተለያዩ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ገብተዋል።

አጥኚዎቹ እንደሚሉት በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ሊያስፈልጋቸው የሚችል ቢሆንም ያንን መጠጣት ላይኖርባቸው ይችላል።

“ምንም እንኳን በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለ አንድ ወንድ በቀን 4.2 ሊትር የውሃ ፍላጎት ቢኖረውም፣ ያን ያህል የውሃ መጠን ግን መጠጣት አያስፈልገውም” ሲሉ ፕሮፌሰር ስፒክማን ተናግረዋል።

በየዕለቱ የምንመገባቸው አብዛኞቹ ምግቦች በውስጣቸው ውሃ ስለሚይዙ ሰውነታችን በቀን የሚያስፈልገውን የውሃ መጠን በቀጥታ ከምንጠጣው ውሃ ባሻገር ከምግቦችም ስለሚያገኝ ይህ ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት አጥኚዎቹ ጠቁመዋል።

ስለዚህም በተለያዩ ቦታዎች እና ሁኔታዎች ውስጥ ለሚገኙ የተለያዩ ሰዎች እንዲሁ በደፈናው በቀን ስምንት ብርጭቆ ወይም ሁለት ሊትር ውሃ መጠጣት አለባቸው ማለት እንደማይገባ ጥናቱ ገልጿል።

“ይህ ጥናት አስካሁን ሁሉም ሰው በቀን ስምንት ብርጭቆ ውሃ መጠጣት አለበት የሚለው ምክር በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ለሚገኙ ብዙ ሰዎች በጣም ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። ይህ ተመሳሳይ የውሃ መጠን መወሰድ አለበት የሚለው የቀደመው ምክር በአሁኑ ጥናት በተገኘው መረጃ የሚደገፍ አይደለም” ብለዋል ፕሮፌሰሩ።

ጥናቱ የዓለማችን ሕዝብ ለወደፊት የሚያስፈልገውን የውሃ መጠን ለማወቅ የሚያግዝ ሲሆን፣ ከሚያስፈልገው መጠን በላይ ውሃ መጠጣትም የሚኖረውን አሉታዊ ውጤትንም አመልክቷል።