በሁለተኛ የማራቶን ውድድሯ ክብረ ወሰን የሰበረችው ትዕግስት አሰፋ

እሁድ መስከረም 15/2015 ዓ.ም. በተካሄደው የበርሊን ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ ትዕግስት አሰፋ የውድድሩን ክበረ ወሰን በመስበር አሸንፋለች።

ትዕግስት የ2022ቱን የበርሊን ማራቶን 2:15:37 በመግባት ነው ያሸነፈችው።

ቀደም ሲል የነበረውን የቦታውን ክብረ ወሰን ሦስት ደቂቃ ያህል በሚደርስ ጊዜ ነው ለማሻሻል የበቃችው።

የቀድሞው የበርሊን ማራቶን ክብረ ወሰን 2:18:11 ሲሆን እአአ በ2018 በኬንያዊቷ ግላዲስ ቼሮኖ የተመዘገበ ነበር።

የትዕግስት ድል ሦስተኛው ፈጣን የማራቶን ሰዓት ለመሆን በቅቷል።

ከእሷ ቀድመው ኬንያዊቷ ብሪጂድ ኮስጌይ (2:14:04) እና እንግሊዛዊቷ ፓውላ ራድክሊፍ (2:15:25) ናቸው የተሻለ ሰዓት ያላቸው።

የ28 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ወደ ውድድሩ የገባችው ብዙም ትኩረት ሳይሰጣት ነው።

ትዕግስት አሰፋ ከዚህ ውድድሩ በፊት በማራቶን የሩጫ ዘርፍ የተወዳደረችው አንድ ጊዜ ብቻ ነበር።

ከበርሊኑ ውድድር ቀድሞ የተሳተፈችው በሳዑዲ አረቢያ በተዘጋጀው የሪያድ ማራቶን ላይ 2:34:00 በሆነ ሰዓት ለማጠናቀቅ ችላለች።

በርሊን ላይ በተካሄደውና ሁለተኛዋ በሆነው የማራቶን ውድድር የራሷን ሰዓት በ20 ደቂቃ ገደማ ለማሻሻል በቅታለች።

እሁድ በተካሄደው ውድር ትዕግስት ከመጀመሪያው ግማሽ ማራቶን ይልቅ በሁለተኛው ግማሽ ማራቶን በፍጥነት መሮጧ ታውቋል።

በዚህ ውድድር ላይ በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን ያሉበትን ቡድን ውድድሩን ከፊት ሲመሩ ቆይቷል።

ከውድድሩ በኋላ ትዕግስት አሁን ያስመዘገበችውን ውጤት ለማምጣት “ዝግጅቴ ጥሩ ነበር” ብላለች።

“ማድረግ ያለብኝን አከናውኛለሁ። ልምምዴ በጣም ጥሩ ነበር። ዛሬ በጣም ደስተኛ ነኝ” ስትል አክላለች።

ለረዥም ጊዜያት የ800 ሜትር ሯጭ የነበረችው ትዕግስት በቅርቡ ነው ወደ ጎዳና ሩጫ ፊቷን ያዞረችው።

በ2016 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክላ በ800 ሜትር ተሳትፋለች። ሆኖም ከግማሽ ፍጻሜው ማለፍ ባለመቻሏ ከውድድሩ ውጪ ሆናለች።

ትዕግስት ከ800 ሜትር በተጨማሪ በ400 ሜትርም ስትወዳደር ቆይታለች።

አትሌቷ ቀደም ሲል ሁለት የግማሽ ማራቶን ውድድሮችን ለማሸነፍ በቅታለች።

በጀርመን (1:07:28) እና በስዊዲን (1:08:20) የተካሄዱ ግማሽ ማራቶኖችን ነው ያሸነፈችው።

በቅርቡም ፈረንሳይ ውስጥ በተካሄደ 10 ኪሜ ውድድር ተሳታፊ ለመሆን በቅታለች።

በውድድሩ ሁለተኛ ስፍራን ለመያዝ ከፍተኛ ፉክክር ተካሂዷል።

ኬንያዊቷ ሮዝመሪ ዋንጂሩ ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች።

ሦስተኛ የወጣችው ኢትዮጵያዊቷ ትዕግስት ናት።

ሁለተኛ እና ሦስተኛ የወጡት የተለያዩት በሦስት ሰከንዶች ብቻ ነው።

ወርቅነሽ ኤደሳ አራተኛ ስትወጣ መሠረት ጎላ አምስተኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

የበርሊን ማራቶን እና ኢትዮጵያውያን

በዓለም አትሌቲክስ ውድድር ውስጥ ከፍተኛ የሚባለው የፕላቲኒየም ደረጃ ያለው የበርሊን ማራቶን እአአ በ1974 ነው የተጀመረው።

በጀርመን መዲና የሚካሄደው ውድድር ፈጣን ሰዓት ከሚመዘገብባቸው የማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ ነው።

ኢትዮጵያውያን አርሌቶች በዚህ ውድድር በተለያዩ ጊዜያት የሰነፉ ሲሆን ኃይሌ ገብረ ሥላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ ቀዳሚዎች ናቸው።

በሴቶች በኩል ጌጤ ዋሚ ውድድሩን ለማሸነፍ የቻለች የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊ ናት።

ጌጤ በ2006 እና በ2007 (እአአ) ውድድሩን በተከታታይ ማሸነፍ ችላለች።

አፀደ ሃብታሙ፣ አበሩ ከበደ፣ ትርፌ ጸጋዬ፣ አሸተ በከሬ እና ጎይትቶም ገብረ ሥላሴ ውድድሩን ማሸነፍ የቻሉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።

በኮቪድ ወረርሽን ምክንያት ውድድሩ እአአ በ2020 አልተካሄደም።

በዘንድሮው ውድድር 55 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ከ120 አገራት ተሳታፊ ሆነዋል።

48ኛውን ቢኤምደብሊው የበርሊን ማራቶን አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በቦታው ተገኝተው ተከታትለውታል ተብሎ ይገመታል።

በወንዶች ምድብ ኬንያዊው ኤሉድ ኪፕቾጌ የርቀቱን ክብረ ወሰን በማሻሻል ቀዳሚ ሆኖ አጠኛቋል።

የ37 ዓመቴ ኬንያዊ ውድድሩን 2:01:09 በሆነ ሰዓት አሸንፏል።

ሌላኛው ኬንያዊ ማርክ ኮሪር ሁለተኛ ሲወጣ ኢትዮጵያዊው ታዱ አባተ ሦስተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።

ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ውድድሩን አራት ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ነው።

ኃይሌ እአአ ከ2006 እስከ 2009 በተከታታይ ለአራት ዓመታት ውድድሩን አሸንፏል።