በሰሜን ኬንያ ከብት ዘራፊዎች በፈጸሙት ጥቃት ፖሊሶችን ጨምሮ 11 ሰዎች ተገደሉ

በሰሜናዊ ኬንያ ከብት ዘራፊዎች በፈጸሙጥ ጥቃት የፖሊስ መኮንኖችን ጨምሮ 11 ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ፖሊስ አስታወቀ።

በጥቃቱ ስምንት ፖሊሶች፣ ሁለት ነዋሪዎች እና አንድ የአካባቢው ባሕላዊ መሪ ቅዳሜ ዕለት ቱርካና ግዛት ውስጥ መገደላቸው ተገልጿል።

ከጥቃቱ በፊት የአገሪቱ ፖሊስ አባላት አንድ መንደርን በመውረር ከብቶችን የዘረፉ ሽፍቶችን ለመያዝ ሲያሳድዱ እንደነበር ተነግሯል።

ፖሊስ ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከአጎራባች የፖኮት ጎሳ አባላት የመጡ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ተጠርጣሪዎቹን ለመያዝ ጥረት እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

እየከፋ በመሄድ ላይ ባለው የአየር ጸባይ ለውጥ ምክንያት በሰሜናዊው ኬንያ ግዛት ውስጥ በከብቶች ዝርፊያ እና በውሃ ምክንያት ግጭቶች ማጋጠማቸው የተለመደ ነው።

ይህ አካባቢ የምሥራቅ አፍሪካ አገራትን በ40 ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ባጠቃው ድርቅ ክፉኛ ከተመቱት ስፍራዎች መካከል አንዱ ነው።

ለአራት ተከታታይ ዓመታት ዝናብ ባለመጣሉ ሳቢያ በድርቁ በተጠቁት አካባቢዎች ውስጥ በርካታ ከብቶች ለሞት እየተዳረጉ ሲሆን ሰብልም ማብቀል አልተቻለም።

በዚህም ምክንያት በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች ምግብና ውሃ ለማግኘት በችግር ላይ ሲሆኑ፣ በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ውስጥ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ለከባድ የረሃብ አደጋ መጋለጣቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አሳውቋል።

ከአስር በላይ የሚሆኑ ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት “በንጹሃን ነዋሪዎች እና በፖሊስ አባላት ላይ የተፈጸመ የፈሪ የወንጀል ድርጊት” ነው ሲል የኬንያ ፖሊስ ጥቃቱን አውግዞታል።

ጥቃት ፈጻሚዎቹን ለመያዝና በቱርካና ግዛት ምሥራቃዊ ክፍል ውስጥ ባለው የገጠር መንደር የተጠናከረ ጥበቃ ለመድግ ተጨማሪ የፖሊስ መኮንኖች ወደ አካባቢው ተሰማርተዋል።