ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሰዎች በፍቅር ግንኙነት ውስጥ አልያም በትዳራቸው ላይ ለምን ይወሰልታሉ?
ትዳር እና ውስልትና እድሜያቸው እኩል ነው።
አንዳቸው የሌላኛቸው ታላቅ ወይንም ታናሽ አይደሉም።
እርስ በእርስ የሚዋደዱ አይመስሉም። ግን አይለያዩም። ለአንዳንዶች ውስልትና አንሶላ መጋፈፍን ይጨምራል፤ ለሌሎች ደግሞ መላከፍ በራሱ የውስልትና መግቢያ በር ነው።
“በትዳር ላይ መወስለት ትዳር የሚባለው ተቋም ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አብሮ የኖረ ጉዳይ ነው” በማለት የምትናገረው የወሲብ እና የፍቅር ጉዳይ አማካሪዋ ኤስተር ፓለር ናት።
ከትዳር ውጪ የሚደረጉ የወሲብ ግንኙነቶች ላይ መጽሐፎችን ያሳተመችው ኤስተር፣ በተለያዩ ማኅበራዊ መድረኮች እና ድረ ገጾች ላይ ንግግሮችን ታደርጋለች።
ሰዎች በትዳራቸው ወይንም በፍቅር ግንኙነታቸው ላይ ለምን ይወሰልታሉ? የሚለውን ጥያቄ ከማየታችን በፊት አንድ ሰው ወሰለተ የሚባለው ምን ሲፈጽም ነው የሚለውን እንፈትሽ።
መወስለት ምንድን ነው?
እንዳልክ አሰፋ የሥነ ልቦና ባለሙያ እና የእርቅ ማዕድ የሥነ ልቦና ማዕከል መስራች ነው።
እንዳልክ እንደሚለው የፍቅር ግንኙነትም ሆነ ትዳር፣ አንዳቸው ለሌኛቸው ለመታመን ተግባብተው የሚመሰርቱት ግንኙነት ነው።
“ይህ ቃል ወይንም ስምምነት ግልጽ እና የሚታወቅ ነው። በተለይ ትዳር ሲሆን፣ በአካል በስሜት በኢኮኖሚ ወይንም በገንዘብ፣ በዓላማ እንዲሁም በመንፈሳዊ አንድነት ለመኖር እንዲሁም ሰጥቶ ለመቀበል የሚደረግ ቃልኪዳን ነው” ይላል።
በዚህ ቃል ወይንም ስምምነት ላይ ሌላ አካል እንዲገባበት ከፈቀድን ይህ ውስልትና ነው በማለት ይገልጻል።
“ወሲብ መፈፀምን ጨምሮ በስሜት ከሌላ ሰው ጋር ግንኙነት መኖር መወስለት ነው። ይኹን እንጂ በሕይወታችን የሚመጡ ሰዎችን ማየት፣ ማድነቅ፣ ችግር አይደለም። ችግሩ የሚመጣው እነዚያን ሰዎች ለወሲብ ከተመኘን እና የራሳችን ለማድረግ ስንፈልግ ነው” ይላል እንዳልክ።
ኤስተር በትዳር ላይ መወስለት በዓለም ሕዝብ ዘንድ የተከለከለ፣ ነገር ግን በሁሉም ባህል እና ማኅበረሰብ ውስጥ ከመተግበር ያልቀረ ነገር ነው ትላለች።
እንደ ኤስተር ከሆነ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ወንዶች ሲወሰልቱ እና ሴቶች ሲወሰልቱ የሚከፍሉት ዋጋ የተለያየ ነው።
“ወሲብ ለወንዶች የሚኮሩበት ጉዳይ ሲሆን፣ ለሴቶች ግን የሚደብቁት እና እንዳልተፈጠረ ቆጥረው የሚያወሩት ጉዳይ ነው።”
አሁን ባለንበት ጊዜ ግን ለውስልት እና አንድ ወጥ ትርጉም መስጠት በጣም አስቸጋሪ መሆኑን ኤስተር ታነሳለች።
ምክንያቱም “ወሲብ ቀስቃሽ የሆኑ አጫጭር መልዕክቶችን በስልክ መላላክ፣ የወሲብ ቪዲዮዎችን መመልከት፣ በድብቅ የፍቅር አገናኝ መተግበሪያዎችን መጠቀም” በአካል ወሲብን ከመፈፀም በተጨማሪ እየተለመዱ የመጡ ጉዳዮች ስለሆኑ ነው።
ኤስተር ለውስልትና ከሰጠቻቸው ብያኔዎች አንዱ የሚከተሉትን ጉዳዮች ይይዛል።
“የድብቅ ግንኙነት፣ ከፍቅር አጋር የማያገኙትን ወይንም የማይጠይቁትን የወሲብ ባህሪ የሚያገኙበት ስፍራ መፈለግ እና መምረጥ ውስልትና ነው።”
‘አንዳንድ ቀንማ ይሻላል ውሽማ’ ለምን?
የሥነ ልቦና ባለሙያው እንዳልክ እንደሚለው ከሆነ ሰዎች ውስልትናን ከልጅነታቸው ጀመሮ በማኅበረሰቡ ውስጥ እየተማሩ የሚያድጉት እንዲሁም ልክ እንደሆኑ ሊያስቡ የሚችሉት ጉዳይ ነው።
“በማኅበረሰቡ ውስጥ እንደ አርዓያ የሚታዩ ሰዎች የጭን ገረድ፣ ቅምጥ፣ ውሽማ እያሉ በትዳራቸው ላይ መሄድን እንደሚያኮራ ጉዳይ ሲወራ እየሰሙ ማደግ፣ በአዋቂነት ሕይወታቸው መወስለትን እንደ ጀብዱ እንዲቆጥሩት እና እንዲተገብሩት ምክንያት ሊሆን ይችላል።”
ይህ ጉዳይ የሚከሰትበት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ የምናገባው አልያም የፍቅር ግንኙነት ያለን ሰው፣ በቁሳዊ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ከሆነ እና የሚያስተሳስር ስሜት ከሌለው ጤናማ ግንኙነት እንዳይኖር ከማድረግ በላይ፣ ለውስልትና ሊያጋልጥ እንደሚችል እንዳልክ ያብራራል።
በተለይ ደግሞ ያገባነው ሰው “ራሳችን ያልመረጥነው ከሆነ ሌላው ውስልትና ሊያመጣ የሚችል ጉዳይ ነው። ሌሎችም ከሰው ሰው ሊለያዩ የሚችሉ በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ” በማለት ይግለጻል።
ኤስተር ግን በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ መሠረታዊ ጉዳይ ትጠይቃለች።
በትዳራቸው ደስተኛ የሆኑ ሰዎች እና የፍቅር ሕይወታቸው እንከን የሌበት እንኳ ሳይቀሩ ለምን ይወሰልታሉ?
ኤስተር እንደምትለው ለምክር እርሷ ጋር ከሚመጡ ሰዎች አብዛኞቹ ለፍቅረኛ በመታመን የሚያምኑ ነገር ግን እምነታቸውን እና ተግባራቸውን ማጣመር እና ማስታረቅ የሚቸገሩ ናቸው።
“በዚህም ለአስርታት ለትዳራቸው ታማኝ የሆኑ ሰዎች፣ የሚወዱትን ሰው እንደሚያጡ እያወቁ ለቅጽበት ደስታ ማለፍ የሌለባቸውን መስመር የሚጥሱት ለምንድን ነው?” ስትል ትጠይቃለች።
ውስልትና የክህደት ተግባር የሚፈፀምበት ተግባር ቢሆንም “በውስጡ ግን ነጻነት፣ የስሜት መተሳሰብ እና ትዳር በመያዝ ያጣነውን ነገር ለማግኘት የምንጣጣርበት ነው” በማለት ትገልጸዋለች።
መወስለት ስህተት ወይስ ምርጫ
የሥነ ልቦና ባለሙያዎች በተግባራችን ሁሉ ውስጥ ምርጫ አለ ይላሉ።
እንዴት? እንዳልክ ይህንን ጉዳይ ሲያብራራ፣ አእምሯችን በምክንያት እና በስሜት የሚሰራ ክፍል እንዳለው በመግለጽ ነው።
“ስለዚህ አንድን ነገር ስንፈጽም ጉዳዩን ደምሮ እና ቀንሶ፣ በጎና ክፉውን የሚነግረን የአእምሮ ክፍል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ውስልትናን ጨምሮ ፍቅር፣ ቅናትን እና ስሜትን የሚገዛ አእምሮ ክፍል አለን።
“ስለዚህ በምክንያት የሚያምነውን ማንነታችንን አሸንፈን እንደዚህ ዓይነት ውስልትናን የመሰለ ተግባርን ስንፈጽም ስህትት ሳይሆን የራሳችን ምርጫ ነው” ይላል።
ኤስተር በበኩሏ የሰው ልጅ የተከለከለውን ነገር የመፈለግ፣ በድብቅ የሚከወን ነገርን የመሻት ሥነ ልቦና እንዳለው ታብራራለች።
አንድ ሰው ውሽማ ይዞ በግልጽ ማሳየት ስለማይችል፣ የተከለከለ ነገር ስለሆነ፣ እንዲሁም የማይቋጭ ጉዳይ በመሆኑ የራሱ ሊያደርገው የማይችለውን ነገር ደጋግሞ እንዲፈልግ ያደርገዋል ስትልም ታክላለች።
ለተወሰለተባቸው መፍትሄው ምንድን ነው?
ኤስተር እንደምትለው መወስለት በፍቅር አልያም በትዳር አጋር ላይ የሚያደርሰው የስሜት እና የሥነ ልቦና ስብራት እንዲሁ በቀላሉ ቸል የማይባል ነው።
እንዳልክ በበኩሉ የተከዳው አካል፣ ወይንም ውስልትና የተፈፀመበት ግለሰብ ፍቅርን እንደተነፈገ፣ የራሱ የሆነን ነገር እንደተነጠቀ እና ዋጋ የሰጠው ነገር ሁሉ እንደረከሰበት ይሰማዋል ሲል ስሜቱን ይገልጸዋል።
አክሎም “ቃል ኪዳን ሲጣስ ልብ አብሮ ይሰበራል። እናም ማንም ሰው የተሰበረ ልብ የሚሰማውን ስሜት በቀላሉ ሊረዳው አይችልም።”
ይህ ያለመፈለግ፣ በሌላ የመቀየር ስሜት ደግሞ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሕይወትን የበለጠ ያወሳስቡታል።
ያኔ ልክ ለታመመ የአካላችን ክፍል ሕክምና ለማግኘት እንደምንሄደው ሁሉ ለተሰበረ ልባችንም መድኃኒት ፍለጋ ግራ ቀኛችንን ማማተር እንደሚያስፈልግ እና ባለሙያ ማማከር ተገቢ መሆኑን አንዳልክ ይጠቁማል።
ኤስተር በበኩሏ የፍቅር ግንኙነት አልያም የትዳር መቃብሩ የውስልትና ደጃፍ ነው ትላለች።
አንዳንዶች በትዳራቸው ላይ ለምን እንደሚወሰለቱ ሲጠየቁ “በግንኙነት ውስጥ ያጡትን ፍለጋ እንደሆነ” እንደሚናገሩ ኤስተር ታስታውሳለች።
አንድ ሰው መወስለቱ በታወቀ ጊዜ ላጠፋው ጥፋት በግልጽ ይቅርታ መጠየቅ ግን ቀዳሚው ነገር መሆን እንዳለበት ትመክራለች።
ይህ የሚሆነው ይቅርታ የሚሰጥ አካል ከተገኘ ብቻ ነው። ካልሆነ በዚህ ግንኙነት ውስጥ መቀጠል አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳቶች አሉት ብሎ ለማቋረጥ የሚወሰን ሊኖር ይችላል።
ጥንዶች አልያም የፍቅር አጋሮች ግን ውስልትና የግንኙነታቸውን በር አንኳኩቶ ሲመጣ የሚወስኑት ውሳኔ ቀድመው ከሚያስቡት የተለየ ሊሆን ይችላል።
የፍቅር አጋሬ በእኔ ላይ ከሄደ እለየዋለሁ የሚሉ ጥንዶች እውነታውን ሲጋፈጡ ያንን ማድረግ አቅቷቸው ታይተዋል።
“አንዳንዴ የትዳር ግንኙነት ማብቂያ ነው፤ ሁሌ ግን አይደለም” ትላለች ኤስተር።
ሁለቱም ባለሙያዎች እንደሚስማሙት ምንም እንኳ ስለ ውስልትና አስቀድሞ ለማውራት ምቹ ሁኔታ ባይኖርም ውስልትና በአንድም በሌላም መልኩ ቢሆን የትዳር አልያም የፍቅር አጋሮችን ማጋጠሙ አይቀርም።
ኤስተር ከወሰለቱት ሰው ጋር የቀደመ ትዳራቸውን አፍርሰው ጎጆ የሚቀልሱ እንደሚኖሩም ገጠመኟን በማንሳት ትጠቅሳለች።
እንዳልክ ደግሞ መገናኛ ብዙኃን አስቀድመው በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት በማድረግ ማኅበረሰቡን ማስተማር ቢችሉ ችግሩን ለመፍታት እንኳ ባይረዳ ግንዛቤ መፍጠር ይችላል ይላል።